መደመር፡ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ መፅሐፍ ኬንያ ገብቷል

የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ "መደመር" መፅሐፍ በኬንያ መዲና ናይሮቢ ተመርቋል።

ናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ነው መፅሐፉን ያስመረቀው። ናይሮቢ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ኬንያውያን እንዲሁም የሌሎች ሃገራት ዲፕሎማቶች የምረቃ ስነ ስርአቱ ታዳሚዎች ነበሩ።

መፅሐፉ እስካሁን ለገበያ የቀረበው በአማርኛና ኦሮምኛ በመሆኑ ከኢትዮጵያውያን ውጭ ሌሎች ዲፕሎማቶች መፅሃፉን ገዝተው ለማንበብ አልቻሉም።

ቢሆንም የመፅሐፉን ይዘት በተመለከተ የጠቅላይ ሚንስትር ፅ/ቤት ባለሟሎች፤ አማካሪዎችና ሌሎችም የፌደራል መስሪያ ቤቶች የስራ ኃላፊዎች በእንግሊዝ አፍ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

መፅሐፉ አሁን ያለውን የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር አጋዥ ነው ይላሉ ማብራሪያ ሰጭዎቹ። ከዚህም በተጨማሪ መፅሐፉ ከተለያዩ እሳቤዎች ሃሳብ ያዋጣ በመሆኑ ሚናው በተግባር የሚለካ ለውጥ ለማምጣት ዕድል ይፈጥራል ባይ ናቸው።

መፅሐፉ በናይሮቢ እንዲመረቅ ያስተባበሩት አምባሳደር መለስ አለም «ኬንያዊያን ጎረቤቶቻችን ሳይሆኑ ወንድሞቻችን ናቸው፤ ለዚህም ነው መፅሐፉን እዚህ እንዲመረቅ የሻትነው» ሲሉ ተደምጠዋል።

«በአሁኑ ወቅት የሚገጥሙን ችግሮች ማንኛውም በለውጥ ሂደት ላይ ያለ አገር የሚገጥመው ችግር ነው» ያሉት አምባሳደሩ ይህንንም በቀላሉ ለማለፍ መደመር መፅሐፍ ድርሻ ይኖረዋል የሚል ሃሳብ አንስተዋል።

መፅሃፋ በኢትዮጵያ በ13 ከተሞች ከሳምንታት በፊት መመረቁ ይታወሳል። ከአገር ውጭ ሲመረቅ ደግሞ ከአሜሪካ ቀጥሎ የናይሮቢው ፕሮግራም ሁለተኛው መሆኑ ነው።

በናይሮቢው የምረቃ ሥነ-ሥርዓት 'መደመር' መፅሐፍ ለገበያ የቀረበ ሲሆን 3 ሺህ የኬንያ ሺልንግ ወይም ደግሞ 30 የአሜሪካን ዶላር ዋጋ ተቆርጦለት ነበር። አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ ገበያ ወደ 890 ብር ገደማ ያወጣል።

ነገር ግን በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ መፅሐፉን የሚገዙ ሰዎች ቁጥር እምብዛም መሆኑን ታዝቧል።

ዋጋው መፅሐፉ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚሸጥበት በ3 እጥፍ የጨመረ መሆኑና መፅሐፉ በሃገር ውስጥ ቋንቋዎች ብቻ ለገበያ መቅረቡ ለሸመታው ማሽቆልቆል ምክንያት ሳይሆን አልቀረም።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ አንባቢዎች የፓርቲ ማኒፌስቶ ሽታ አለው ሲሉ ከገመገሙት 'መደመር' ባሻገር፤ 'ዲርአዝ' በተሰኘ የብዕር ስም አራት የታተሙ ሁለት ያልታተሙ መጽሐፎች እንዳሏቸው መናገራቸው ይታወሳል።