ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች የደረሱት ሥምምነት ምንድን ነው?
በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ እና በርካታ ደጋፊ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አብረው ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።
የፊርማ ስምምነቱ የተካሄደው ማክሰኞ መስከረም 20/2012 ዓ.ም ሲሆን በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በስምምነቱ ላይ በዋናነት ከተገኙና ፊርማቸውን ካኖሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ አንድነትና ነፃነት ግንባር፣ እና ሌሎችም ይገኙበታል።
በዕለቱ "እርስ በእርሳችን ሰላም ከሌለን እንዴት ለሌሎች ሰላም መስጠት እንችላለን?" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቀራርቦ መወያየቱ ወደፊት ለመጓዝ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
መጪው ምርጫ ያለምንም ጥርጥር ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ እንደሚሆንም ተናግረዋል።
በኦዲፒ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት የመከላከያ ሚኒስትሩና የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ ሲሆኑ የአቋም መግለጫውን ደግሞ ጃዋር መሃመድ ነበር በንባብ ያሰማው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ "ከመካሰስና እርስ በእርስ ከመነቋቆር ወጥተን እንደ 21ኛው ክፍለ ዘመን ሰው ቁጭ ብለን ተነጋግረን መስራት አለብን" ብለዋል።
ምን ምን ጉዳዮች ላይ ተስማሙ?
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ስምምነት ላይ የደረሱት በተናጠልና በጋራ ላለፉት አምስት ወራት በጉዳዩ ላይ ውይይት ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ መሆኑን ገልፀዋል። ከውይይቱም በኋላ በዋናነት ትግል በሚሹ ጉዳዮች ላይ በአንድነት መሥራት የሚያስችል አደረጃጀት ለማኖር መስማማታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት የኦሮሞ አመራር ጥላ የተሰኘ የጋራ መድረክ የተቋቋመ ሲሆን፣ ይህንን አደረጃጀት አቶ ለማ መገርሳ በኃላፊነት ሲመሩት፣ አቶ ሌንጮ ለታ፣ አቶ ገላሳ ዲልቦ እና ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) ደግሞ አማካሪዎች በመሆን ተሰይመዋል።
የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ጃዋር መሀመድና አቶ አበራ ቶላ የዚህ አደረጃጀት አስተባባሪዎች ሆነው ተመርጠዋል።
በዕለቱ ስምምነት ከተፈረመባቸው ሌሎች ነጥቦች መካከልም ስምምነቱን በፈረሙት ፓርቲዎች መካከል አለመግባባትና ቅሬታዎች ካሉ ወደ ተቋቋመው አደረጃጀት በማምጣት ጉዳያቸውን በንግግርና በውይይት እንዲፈቱ የሚል ይገኝበታል።
እንዲሁም ኦሮሚያ ውስጥ ባለው አለመግባባትና ግጭት እየጠፋ ያለውን የሰው ሕይወትና ንብረት በአስቸኳይ ማስቆም የስምምነቱ አንድ አካል ነው ተብሎ ተጠቅሷል።
መጪው ምርጫ ነፃና ፍትሃዊ እንዲሆን በጋራ መስራት ላይም ተስማምተው ፊርማቸውን ማኖራቸውን በዕለቱ ተገልጿል።
በጉዳዩ ላይ ማን ምን አለ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ኦነግ የትጥቅ ትግሉን በመተውና በሰላም ለመታገል በመወሰን ወደ ሀገር ከገባ በኋላ ከኦዲፒ ጋር ስምምነት ላይ ደርሶ ነበር።
ነገር ግን ይህ ስምምነት ውጤታማ ሳይሆን ፓርቲዎቹ ወደ አለመግባበት በመግባታቸው፣ አባ ገዳዎች፣ አደ ሲንቂዎችና የፖለቲካ ምሁራን በተገኙበት ዳግመኛ ስምምነት እና እርቅ ቢወርድም ይህም ብዙም ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል።
ይህ የአሁኑ ስምምነትም ብዙ ላይዘልቅ ይችላል በሚል አንዳንዶች ጥርጣሬ እንዳደረባቸው በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን ላይ ሲናገሩ ይደመጣል።
የአዲሱ አደረጃጀት ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ለማ መገርሳ ግን የአሁኑ ስምምነት ከዚህ በፊት ከተደረሱት ስምምነቶች የተለየ ስለመሆኑና ተስፋ ሰጪ መሆኑን ይናገራሉ።
"ምክንያቱም ከጥርጣሬ እና ከመወነጃጀል ወጥተን በቅን ልቦና ስለተነጋገርን፣ ይህ ስምምነት ለእኔ ተስፋ ሰጥቶኛል" ያሉት አቶ ለማ አክለውም ''አጀንዳችን የኦሮሞ ሕዝብ አጀንዳ ስለሆነ ቢመቸንም ባይመቸንም ቁጭ ብለን በጋራ መነጋገር አስፈላጊ መሆኑ ላይ ተግባብተናል'' ብለዋል።
ስምምነቱ ጥንቅቅ ያለ ነው አይባልም ያሉት አቶ ለማ ውይይቱን ማጠናከርና በኦሮሞ ፓርቲዎች መካከል አንድ የጋራ ግንባር መፍጠር አስፈላጊ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
አለመግባባቶችና የሚያቀያየሙ ነገሮች እንኳ ቢኖሩም ትልቁን የኦሮሞ ሕዝብ ጥቅም በማስቀደም ነገሮችን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲጠናከርም አሳስበዋል።
ማክሰኞ መስከረም 20/2012 ዓ.ም የስምምነት ፊርማቸውን ያኖሩ ፓርቲዎች በጋራ በመሆን ሐሙስ ምሽት መግለጫ ሰጥተዋል።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ሕዝባችን በጋራ አንድነቱን ጠብቆ ለውጡን እንዳመጣ ሁሉ እንዲሁ አንድነቱን ጠብቆ ወደፊት ማስቀጠል ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም በኦሮሞ ፓርቲዎች እንዲሁም የፖለቲካ ሰዎችና ምሁራን መካከል ያለው መለያየትም በዚህ አደረጃጀትና ስምምነት መሰረት ትክክለኛ መስመር መያዙን ተናግረዋል። "ይህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት" ሲሉም አሳስበዋል።
የኦሮሞ አንድነትና ነፃነት ግንባር ሊቀመንበር ብርጋዴር ጄነራል ከማል ገልቹ በበኩላቸው የሕግ የበላይነትንና የሀሳብ ነፃነትን በማክበር በጋራ መስራት ይቻላል ብለዋል።
የሀሳብ ልዩነት እንኳ ቢኖር በመከባበር በጋራ መስራት ያስፈልጋል ያሉት ጄነራሉ፣ አክለውም በኦሮሞ ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት የሁላችንም ስለሆነ በፍጥነት መፈታት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም ተጠብቆ ዲሞክራሲያዊ መሆኑ የሁሉ ችግር መፍትሄ ነው ብለዋል።
በዚህ ሂደት ውስጥ የኦሮሞ ፓርቲዎች አንድ አቋም ይዘው በጋራ መስራት፣ ብሔር ብሔረሰቦችም ይህንኑ ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝምን ተቀብለው ሊተገብሩት እንደሚገባ ተናግረዋል።
አቶ ሌንጮ ለታ በበኩላቸው ለረዥም ጊዜ የኦሮሞ ፓርቲዎችን ወደ አንድ ለማምጣት ሲታገሉ እንደነበር ገልፀው አሁን በመሳካቱ "እድለኛ ነኝ" ብለዋል።