ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
10 ሚሊዮን ሕዝብ ይታደምበታል የተባለው ኢሬቻ በአዲስ አበባ
በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ እና የተለያዩ ሃይማኖቶችን የሚከተሉ ኦሮሞዎችን የሚያገናኘው የኢሬቻ በዓል በመጪው ቅዳሜ በአዲስ አበባ፤ እሁድ ደግሞ በቢሾፍቱ በድምቀት ለማክበር የተለያዩ ዝግጅቶች መደረጋቸው ተገልጿል።
ይህ የኢሬቻ ክብረ በዓል በኦሮሞዎች ዘንድ ከሚከበሩ የተለያዩ ክብረ በዓላት መካከል አንዱ ሲሆን፣ በትውልዶች መካከል ሲወርድ እንደመጣ ይነገራል፡፡
በዓሉ በአዲስ አበባ መከበር ካቆመ 150 ዓመታት እንዳለፉት የሚናገሩት አባገዳዎች ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በከተማዋ ላይ ሊከበር መሆኑ ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል።
ከ150 ዓመት በኋላ በአዲስ አበባ የሚከበረውን ኢሬቻ ለማክበርም ከኦሮሚያ ከልል ሁሉም ዞኖች ታዳሚዎች ወደ አዲስ አበባ እየተመሙ መሆኑነን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰቦች ይገልፃሉ።
ከእነዚህም መካከል አንዱ የሆነው የሐረሩ ነገዎ መገርሳ ከሚኖርባት ጃርሶ ወረዳ፣ አፍረን ቀሎ ከተማ ተነስቶ ነጭ ባንዲራ በመያዝ ወደ አዲስ አበባ መጥቷል።
ነገዎ ከሚኖርባት ከተማ መስከረም 10/2012 ዓ.ም የተነሳ ሲሆን ዘጠኝ ቀንና ለሊት በእግሩ ተጉዞ አዳማ ከደረሰ በኋላ ቢቢሲ አግኝቶ አነጋግሮታል።
ነገዎ አዲስ አበባ ድረስ በእግሩ ለመጓዝ የፈለገው ኢሬቻ ከ150 ዓመት በኋላ በሀገሪቱ መናገሻ ከተማ አዲስ አበባ መከበሩን በማስመልከት እንደሆነ ይገልፃል።
በየደረሰበት ከተማ ነዋሪው መልካም አቀባበል እንዳደረገለት የሚናገረው ነገዎ፤ አዲስ አበባ ሲደርስ አምስት የኦዳ (ዋርካ) ዛፍ ችግኝ እንደሚተክል ተናግሯል።
ነገዎ ከዚህ ቀደም 30 ሺህ የዛፍ ችግኞችን በማፍላት በተለያዩ ክልሎች መትከሉን ገልጾ አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ አምስቱም የመግቢያ በሮች ለመትከል ማቀዱን ይናገራል።
ዝግጅቱ ምን ይመስላል?
ዕረቡ ዕለት የኦሮሚያ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ እሬቻን በአዲስ አበባ (ሆረ ፊንፊኔ) በደመቀ ሁኔታ ለማክበር የሚያስችል ቅድመ ሁኔታ መጠናቁቅን በማስመልከት መግለጫ ሰጥቷል።
ከ150 ዓመት በኋላ በአዲስ አበባ ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል የኢሬፈና (ምስጋና የማቅረብ ሥነ ሥርዓት) ስፍራ በፍል ውሃ አካባቢ እንደሚሆን ተለይቶ አካባቢውን የማስተካከል ሥራ መሰራቱንም ጨምሮ ገልጿል።
በዚህ በዓል ላይ ለመታደም ከአማራ፣ ከትግራይ፣ ከአፋር፣ ከሱማሌ፣ ከደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝና ሌሎች ክልሎች የሚመጡ ተሳታፊዎች እንደሚኖሩም ተገልጿል።
በዋዜማው መስከረም 23፤ የተለያዩ ዝግጅቶች የይኖራሉ ያለው ቢሮው ከእነዚህ መካከል አራት ሺህ ሜትር የሚረዝም ጭኮ፣ የሙዚቃ ድግሶች በሚሌኒየም አዳራሽና በስታዲየም፣ እንዲሁም የሲዳማ የቄጠላ ባህል (ባህላዊ ጭፈራ) ይቀርባል ሲሉ ጨምረው አስረድተዋል።
አክለውም በመስቀል አደባባይ የጭኮ ዐውደ ርዕይ፣ የቄጠላ ጭፈራ፣ የፈረስ ጉግስ እንዲሁም ሌሎች የባሕላዊ ምግቦችና አልባሳት ትርዒት እንደሚኖር በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
ክብረ በዓሉ ላይ ከሁሉም የኦሮሚያ ዞኖች ተሳፈታፊዎች ወደ አዲስ አበባ መጓዝ የጀመሩት ከቀናት በፊት መሆኑን በማስታወስም በአጠቃላይ 10 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ ይታደማል ተብሎ እንደሚጠበቅ በመግለጫው ወቅት ተነግሯል።
በዓሉ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ከ15 እስከ 20 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች [ፎሌዎች] እንደሚሳተፉ የተገለፀ ሲሆን የሰላም ማስከበሩን ሥራ በኃላፊነት የሚሰራ ኮሚቴም ተዋቅሯል ተብሏል።
በትናንትናው ዕለትም የኢሬቻ በዓልን ምንነት ማስረዳት ላይ ያተኮረ ፎረም በሸራተን አዲስ ተካሂዷል።
በፎረሙ ላይ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ ምሁራንና አባገዳዎች ጥሪ ከተደረገላቸው እንግዶች ጋር የታደሙ ሲሆን የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር የሆኑት ሒሩት ካሳው ባደረጉት ንግግርም "የብሔር ብሔረሰቦች ባህል ከሌለ የኢትዮጵያ ባህል የምንለው አይኖርም" ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም የሕዝቦችን መቀራረብ ለማጠናከርና የሀገሪቱን ቱሪዝም ለማበረታታት ይህንን መሰሉ ባህላዊ ፌስቲቫሎች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
አባ ገዳዎችና አደ ሲንቄዎች የኢሬቻ ባህልን ጠብቀው ወደዚህ ትውልድ በማስተላለፋቸው አመስግነው፤ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ደግሞ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግረዋል።
4000 ሜትር የሚረዝም ጭኮ
የኦዳራ ኢንተርናሽናል ካፌ ባለቤት የሆኑት አቶ ድንቡ አብደላ፤ የኢሬቻ ክብረ በዓል ወደ አዲስ አበባ መመለሱን አስመልክተው "የድርሻዬን ልወጣ ብዬ ነው" በማለት እስካሁን 'ረዥሙ ነው' የተባለውን ጭኮ ለማዘጋጀት መነሳታቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ጭኮን ለምን እንደመረጡ ሲያስረዱም "ይህ ትልቅ ሕዝብ ምን ባህላዊ ምግብ አለው? በምን ይታወቃል? ብለን አምስት ባህላዊ ምግቦችን ከዘረዘርን በኋላ ጭኮ በድሮ ጊዜ በጦርነት ወቅት እንደ ስንቅ ተይዞ የሚኬድ ስለነበር፣ ከዚያ አንጻር መርጠነዋል" ብለዋል።
ይህን 4 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ጭኮ ለማዘጋጀት 49 ኩንታል ገብስ፣ 3538 ኪሎ ግራም ቅቤ ጥቅም ላይ መዋሉን አቶ ድንቡ ነግረውናል።
በቀን 300 ሜትር ያህል ጭኮ ሲሰራ መሰንበቱን የሚናገሩት ባለሀብቱ፤ በሥራው 18 ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን ሥራውም 29 ቀናት እንደፈጀ ገልፀዋል።
ይህንን ረዥም ጭኮ በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ለማስመዝገብ መታሰቡንም የሚናገሩትወ አቶ ድንቡ፤ ይህን ጭኮ መንግሥት ወጪውን ሸፍኖ ለተሳታፊዎች በነፃ የማያቀርብ ከሆነ እነርሱ በተመጣጣኝ ዋጋ በእለቱ ለመሸጥ ማሰባቸውን ገልጸዋል።
ይህንን ጭኮ ለማዘጋጀት ምን ያህል ገንዘብ እንዳወጡ ባለሀብቱ አልተናገሩም።
ባንዲራና ኢሬቻ
በአዲስ አበባም ሆነ በቢሾፍቱ በሚከበረው የኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ ከአባ ገዳ ባንዲራ ውጪ የየትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ባንዲራ እንዳይያዝ የበዓሉ አስተባባሪ ኮሚቴ እና የቱለማ አባ ገዳ የሆኑት ጎበና ሆላ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አባ ገዳው አክለውም ባንዲራው የግጭት መንስዔ እንዳይሆንና ኢሬቻ ከፖለቲካ እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች በላይ ስለሆነ እንዳይቀላቀል ሲሉ ውሳኔውን ማሳለፋቸውን በቃለ መጠይቁ ወቅት አብራርተዋል።
ከዚህ ቀደም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ባንዲራ የኦሮሞ ሕዝብ የትግል ዓርማ ተደርጎ ይወሰዳል። ከዚህ በፊትም ቢሾፍቱ ላይ ሲካሄድ በነበረው የኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ ክልክል ሆኖ ይዞ የተገኘ ግለሰብ በሕግ ይጠየቅ እንደነበር ይታወሳል።
በጉዳዩ ላይ የበዓሉ ተሳታፊዎች ባንዲራውን መያዝ በመከልከላቸው ደስተኛ አለመሆናቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።
በበዓሉ ወቅት የሚደረጉ የሰላም ማስከበር ሂደቶችን በተመለከተ የአዲስ አበባና ኦሮሚያ ፖሊስ እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ ቀደም ብለው መግለጫ ሰጥተዋል።