ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የመስቀል ደመራ አከባበር ውዝግብ በቢሺፍቱ ከተማ
ትናንት ከኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ተነስተው፤ ወደ ደመራ ለመሄድ መንገድ ላይ ሳሉ፤ "ያልተፈቀደ ሰንደቅ አላማ ይዛችኋል" በሚል ማለፍ መከልከላቸውን የቢሾፍቱ ኪዳነ ምሕረት አገልጋዮችና ምዕመናን ለቢቢሲ ተናገሩ።
የዓደአ ወረዳ ቤተክህነት ጸሀፊ መጋቤ ጥበብ እውነቱ ጥላሁን፤ ከደመራው ዕለት ቀደም ብለው ከከተማው አስተዳደር ጋር በበዓሉ አከባበር ዙሪያ ለመነጋገር ስብሰባ ቢያደርጉም ባለመግባባት እንደተለያዩ ያስታውሳሉ።
የኢሬቻ እና የመስቀል በዓል በሰላም እንዲያልፍ ከአድባራት ኃላፊዎች፣ ከምንጣፍ አንጣፊ ማኅበራት እና ከሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ጋር በመሆን ውይይት ተካሂዶ እንደነበር የሚያስታውሱት ጸሀፊው፤ "ልሙጥ ባንዲራ መያዝ ትችላላችሁ፣ አትችሉም" የሚለው ውይይት ላይ የሌሎች እምነት ተከታይ ኃላፊዎች መሳተፋቸው እንዳላስደሰታቸው ይናገራሉ።
ከዚህ ስብሰባ በኋላ ግን፤ የከተማው ከንቲባ ጠርተዋቸው ይቅርታ እንደጠየቋቸውና በሰንደቅ አላማ ጉዳይ ተነጋግረው፤ ልሙጥ (ኮከብ የሌለው) ባንዲራ መያዝ በሕግ ስለማይፈቀድ፤ ይዘው መውጣት እንደሌለባቸው መስማማታቸውን ይናገራሉ። የበዓል ማድመቂያ ሪቫኖችን ግን በአደባባይ ላይ አስረው በዓሉ በድምቀት እንዲከበር እንደተስማሙ ያክላሉ።
መላከ ሰላም አባ ሩፋኤል በቢሾፍቱ የደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ሲሆኑ፤ የመስቀል በዓልን ለማክበር በቢሾፍቱ የሚገኙ አድባራት በአጠቃላይ ወደ መስቀል አደባባይ እንደሚወጡ አስታውሰው፤ ሁሉም ቤተክርስቲያናት በወጣላቸው መርሃ ግብር መሰረት ወደ መስቀል አደባባይ መምጣታቸውን ይገልፃሉ።
ሆኖም ግን የደብረ መፅሔት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያንን የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት የለበሱት ልብስ ላይ "ልሙጥ ባንዲራ አለበት" ያሉ የአካባቢው ወጣቶች፤ ዝማሬ የሚያሰሙትን የዕምነቱን ተከታዮች አታልፉም ብለው እንደከለከሏቸውና ወደ መስቀል አደባባይ መሄድ አንዳልቻሉ መላከ ሰላም አባ ሩፋኤል ይናገራሉ።
የሰንበት ትምህርት ቤቱ አባል የሆኑ አንድ ግለሰብ ለቢቢሲ እንዳረጋገጠው፤ ትናንት ከኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ተነስተው ወደ ቢሾፍቱ መስቀል አደባባይ መሄድ የጀመሩት ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ነው።
በግምት ከቤተክርስቲያኒቱ 500 ሜትር እንደራቁ፤ የተወሰኑ ወጣቶች "የለበሳችሁት ባንዲራ የተከለከለው ነው" በሚል እንዳስቆሟቸው ይናገራል።
"በመጀመሪያ እነዚህን ወጣቶች እየዘመርን አልፈናቸው ነበር" የሚለው የሰንበት ትምህርት ቤቱ አገልጋይ፤ በኋላ ግን የቀበሌ 5 አስተዳደር ፖሊስ ይዘው ሄደው መንገዱን እንደዘጉትና ለሰዓታት ቆመው መከራከራቸውን ይናገራል።
"የለበስነው የመዘምራን ልብስ ድሮም እንጠቀምበት የነበረ፣ ቆቡም ድግድጋቱም አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ነው። ይህንን ካላወለቃችሁ አታልፉም አሉን" ሲል በወቅቱ የነበረውን ይናገራል።
ቤተክርስተያን ቀለሙን ለዘመናት ስትጠቀምበት መኖሯን የሚገልፁትና "ይህ ምልክት የቀስተ ደመና ምልክት፣ ከመስቀሉ በፊት ነበረ፣ የኖህ ቃል ኪዳን የዳግመኛ አለመጥፋት ምልክት ነው" የሚሉት ደግሞ የወረዳው ቤተ ክህነት ጸሀፊ ናቸው።
አትሄዱም ብለው ያስቆሟቸው የፀጥታ አካላት፤ ሰንደቅ አላማውን ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በማዛመድ "የአብን ነው፣ የኢዜማ ነው" ብለው እንዳንገላቷቸው የሚናገረው የሰንበት ትመህርት ቤቱ አገልጋይ፤ እነርሱም አናወልቅም በማለት መስቀል አደባባይ መሄዳቸውን ትተው ወደ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን መመለሳቸውን ይናገራል።
ይህ አገልጋይ "27 ዓመት በቤተክርስቲያኒቱ ሳገለግል ተከልክለን አናውቅም ዘንድሮ መከልከላችን አዲስ ነው" ይላል።
የኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን መዘምራንና ምዕመናን አለመምጣታቸውን ያስተዋሉ ወደ መስቀል አዳባባይ የሄዱት ሰዎች፤ "አንድ ደብር ጎሎ ደመራ አናበራም" ብለው ወደ ኪዳነ ምሕረት መሄዳቸውን የሚናገሩት ደግሞ መላከ ሰላም አባ ሩፋኤል ናቸው። በዚህም የተነሳ በቢሾፍቱ መስቀል አደባባይ ደመራውን ሳያበሩ መቅረታቸውን ተናግረዋል።
የፖሊስ ኃላፊው አናግረው "ምዕመኑ ይመጣሉ" መባላቸውን የሚያስታውሱት መላከ ሰላም አባ ሩፋኤል፤ ሳይመጡ ሲቀሩ የተወሰኑ አድባራት አስተዳዳሪዎች ከመስቀል አደባባይ ተነስተው ወደ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ምዕመናኑን ለማምጣት ማምራታቸውን አስታውሰዋል።
የአድባራቱ አስተዳዳሪዎች የኪዳነ ምሕረት ምዕመናንን አሳምነውም ወደ መስቀል አደባባይ ለመውሰድና ደመራው እንዲበራ ለማድረግ ጥረት ቢያደርጉም ስላልተሳካ፤ ወደ መስቀል አደባባይ በመመለስ ትምህርተ ወንጌል ተሰብኮ፣ ፀሎት ተደርጎ፣ ወደ ቡራኬ ሊኬድ በሚባልበት ሰዓት፤ በመስቀል አደባባይ የተገኘው ምዕመን "ኪዳነ ምሕረቶች ሳይመጡ ዳመራው አይለኮስም" በማለቱ ምክንያት ፀሎት ተደርጎ፣ ደመራው ሳይለኮስ ትተው እንደሄዱ የዓደአ ወረዳ የቤተክህነት ፀሀፊ እና የደብረ ገነት ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ኃላፊዎቹ አክለውም ፤ "ዛሬ ማለዳ እንዳየነው ግን ደመራው ተቃጥሏል፤ ማን እንዳደረገው አናውቅም" ብለዋል።
የወረዳው የቤተክህነት ጸሀፊ አክለውም፤ ትናንት እንዲህ አይነት ችግር የታየው በኪዳነ ምሕርት ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ቢሾፍቱ አፋፍ ደብረ ስብሃት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲይን ጭምር መሆኑንም ይገልፃሉ።
የአካባቢው የምንጣፍ አንጣፊ ማኅበራት፤ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ላይ የሥላሴና የቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ያለበት ካናቴራ እንዲያወልቁ መደረጋቸውን ይናገራሉ።
ይህንን ካናቴራ አምና ወጣቶቹ ለጥምቀት በዓልም ተጠቅመውበታል የሚሉት ፀሀፊው፤ ትናንት ግን በፀጥታ አካላት በመከልከላቸው ነጠላ ለብሰው ወደ መስቀል አደባባይ መምጠታቸውን ይናገራሉ።
ዛሬ ማለዳ የምሥራቅ ሸዋ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የተፈጠረውን ሰምተው፤ ወደ ቢሾፍቱ ደብረ መዊ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሄደው ምዕመናኑን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላቶችን እና የሀይማኖት አባቶችን በማነጋገር እያረጋጉ መሆኑን በስፍራው የተገኙት ኃላፊዎቹ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ ደመራው ትናንት መለኮሱን አረጋግጦ፤ ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት ግን መረጃ መሰብሰብ እንዳለበት ገልጾልናል።
የከተማዋ ከንቲባ ስልክ ባለመስራቱ በጉዳዮ ላይ ምላሻቸውን ማግኘት አልቻልንም።