አሜሪካ ከግብፅ የተሰረቀውን የወርቅ ሬሳ ሳጥን መለሰች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ ሙዚየም ከግብፅ ተዘርፎ የነበረውን በወርቅ የተለበጠ ሬሳ ሳጥን ለግብፅ መለሰ።
ሬሳ ሳጥኑ ከግብፅ የተዘረፈው በ 'አረብ ስፕሪንግ' አብዮት ወቅት ነበር። ኒው ዮርክ ለሚገኘው ሜትሮፖሊታን ሙዚየም ቅርሱን ሲገዛ፤ ከግብፅ ተዘርፎ የተወደ መሆኑን እንዳላወቀ ተገልጿል።
ሙዚየሙ፤ ከክርስቶስ ልደት በፊት በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ እንደተሠራ የሚገመተውን ሬሳ ሳጥን ለግብፅ ባለሥልጣኖች አስረክቧል።
ሬሳ ሳጥኑ ውስጥ ኔደጅማንክህ የተባሉት እና ሔሪሻፍ የተባለው አማልክት ቄስ የደረቀ አስክሬን እንደሚገኝበት ተገልጿል።
ሙዚየሙ የወርቅ ሬሳ ሳጥኑን የገዛው ከሁለት ዓመት በፊት፤ በ4 ሚሊየን ዶላር ነበር። ሬሳ ሳጥኑን ማዕከል ያደረገ አውደ ርዕይም በሙዚየሙ ተካሂዷል።
የተዘረፉ ቅርሶችን የሚመረምር የአሜሪካ ፖሊስ ሬሳ ሳጥኑ የተሰረቀ መሆኑን ከደረሰበት በኋላ ሙዚየሙ ቅርሱን ለመመለስ ወስኗል።
የማንሀተን አቃቤ ሕግ ሳይረስ ቪንስ፤ "ይህን ሬሳ ሳጥን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥንታዊ ቅርሶች መዘረፋቸውን ደርሰንበታል" ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል። ቅርሶቹን በሕገ ወጥ መንገድ የሚያዘዋውር አንድ ቡድን እንዳለም ጠቁመዋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2011 ግብፅ ውስጥ አብዮት ሲቀጣጠል፤ ሬሳ ሳጥኑ ሚንያ ከሚባለው አካባቢ ተዘርፎ፤ በዱባይ በኩል ወደ ጀርመን ከዛም ወደ ፈረንሳይ ተወስዷል።
ፈረንሳይ፣ ፓሪስ ውስጥ የሚኖር የሥነ ጥበብ ደላላ 6 ጫማ የሚሆነውን ሬሳ ሳጥን ለሙዚየሙ ሸጧል።
ቅርሱ በይፋ ለግብፅ በተመለሰበት ሥነ ሥርዐት ላይ የግብፅ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር፤ ቅርሱ የግብፅ ብቻ ሳይሆን የመላው የሰው ልጅ ነው ብለዋል።












