ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የወንድ ልጅ የዘር ፍሬን ሙቀት የለካው ምርምር ተሸለመ
በዘንድሮው የስፑፍ ኖቤል ሽልማት ላይ ካሸነፉ የምርምር ሥራዎች መካከል በግራና በቀኝ የዘር ፍሬዎች መካከል የሙቀት መጠን ልዩነት መኖር አለመኖሩን ለማወቅ የተደረገው ጥናት ይገኝበታል።
ተመራማሪዎቹ በዚህ ጥናታቸው የወንድ ልጅን የቀኝና የግራ ዘር ፍሬ ሙቀት በመለካት ልዩነቱን ለማወቅ ጥረዋል። በአጠቃላይ 22 ወንዶችን ለዚህ የምርምር ሥራ የተጠቀሙ ሲሆን፤ ግለሰቦቹ የፖስታ ቤት ሠራተኞችና የአውቶቡስ አሽከርካሪዎች ናቸው ተብሏል።
ምርምሩ የተካሄደው እርቃናቸውን እንዲሁም ልብስ ለብሰው በቆሙ የፈረንሳይ ፖስታ ቤት ሠራተኞች ላይ ነው።
በዚህ ምርምር፤ የግራ የዘር ፍሬ ከቀኙ ይልቅ እንደሚሞቅ ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል ተመራማሪዎቹ። ይህ ግን የሚሆነው ልብስ ከለበሱ ብቻ ነው ይላሉ።
ምርምሩ የተደረገው በ11 የፖስታ ቤት ሠራተኞች ላይ ሲሆን፤ ለ90 ደቂቃ ያህል ቆመው የዘር ፍሬያቸው ሙቀት መለካቱንም ለማወቅ ተችሏል። የፖስታ ቤት ሠራተኞቹ የዘር ፍሬ የሙቀት መጠን በየሁለት ደቂቃው የተለካ ሲሆን፤ የግራ የዘር ፍሬ ሙቀት መጠን ከቀኙ ከፍ ብሎ ታይቷል።
11 የአውቶቡስ ሹፌሮች ተቀምጠውም የዘር ፍሬ ሙቀት የተለካ ሲሆን፤ የምርምር ውጤቱ የሕክምና ምርምር ሥራዎች በሚታተምበት መጽሔት ላይ እንደወጣ ተነግሯል።
በዚህ ምርምር ማረጋገጥ እንደተቻለው የዘር ፍሬ ሙቀት የወንዶች የመውለድ አቅም ላይ ተጽዕኖ አለው።
በምዕራቡ ዓለም የወንዶች የዘር ፈሳሽ ጥራት መቀነስ የታያ ሲሆን፤ ይህንን ለማሻሻል የተደረጉ ጥናቶች በቁጥር አናሳ ናቸው።