የስኮላስቲክ አፕቲቲዩድ ፈተና ውጤትን የሚያጣራ ኮሚቴ ተዋቀረ

የከፍተኛ ተቋም መግቢያ ፈተና ውጤት

የፎቶው ባለመብት, TIKVAH-ETH

በዘንድሮው የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ አንዳንድ ተማሪዎች የ ስኮላስቲክ አፕቲቲዩድ (ሳት) ፈተና ውጤታቸው ላይ ቅሬታ እያሰሙ ነው።

በድሬዳዋ ከተማ የተለያዩ የመሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የነበሩና ውጤታቸው ላይ ቅሬታ ያላቸው ተማሪዎችና ወላጆች ዛሬ ወደ ትምህርት ቢሮ ማምራታቸውን ገልጠው የትምህርት ቢሮ ኃላፊዋ ቅሬታቸውን ለበላይ ኃላፊዎች በአካል በመሄድ እንደሚያቀርቡ እንደነገሯቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በድሬዳዋ ቅድስት ቤዛ የመሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነችውና ለቢቢሲ ቅሬታዋን ያቀረበችው ተማሪ አጠቃላይ ሌሎች የትምህርት አይነቶች ላይ ቅሬታ ቢኖራትም የስኮላስቲክ አፕቲትዩድ ውጤቷ ግን ከሚጠበቀው በታች እንደሆነ ታስረዳለች።

"የእኔ 35 ነው ከመቶ፤ የጓደኞቼም ሐያ እና ከዚያ በታች ነው" በማለት በአጠቃላይ ውጤት 400ና ከዚያ በላይ ያመጡ ተማሪዎችን ውጤት በማጣቀስ ያለውን ልዩነት ታሳያለች።

ዛሬ በድሬዳዋ ትምህርት ቢሮ ተገኝተው ቅሬታቸውን ያቀረቡት ወላጆችና ተማሪዎች የሮትቶዳም፣ ብስራተ ገብርዔል፣ እና የቤዛ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና የተማሪ ወላጆች እንደሆኑ ለማወቅ ችለናል።

የመቀሌ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ተማሪ በበኩሏ በሌሎች የትምህርት አይነቶችም ባመጣችው ውጤት ጭምር ደስተኛ አለመሆንዋን ትናገራለች።

የአፕቲትዩድን ውጤቷም ቢሆን ከጠበቀችው በታች መሆኑን በመናገር "አፕቲትዩድ ላይ ተሸላሚ ተማሪ ሳይቀር ነው ዝቅተኛ ውጤት ያመጣው። እንዴት ብሎ ነው አንድ ተማሪ 6፣ 7፣ 0 ከ100 የሚያገኘው?" ስትል ትጠይቃለች።

"እኔ ለፈተናው ካደረግኩት ዝግጅት አንጻር ያገኘሁት ውጤት ፈጽሞ አይመጥነኝም" በማለትም ቅሬታዋን ለቢቢሲ ገልጣለች።

የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ

የፎቶው ባለመብት, NEAA FACEBOOK

ተማሪዎቹ ያቀረቡትን ጥያቄ መስማታቸውን የሚናገሩት የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አርአያ ገ/እግዚአብሔር ቅሬታው እንደደረሳቸው ለቢቢሲ አረጋግጠው ለማጣራት ኮሚቴ ማዋቀራቸውን ተናግረዋል።

አሁን እያስተናገድን ነው ያሉት አቶ አርአያ ማንኛውም ቅሬታ ያላቸው ተማሪዎች ቅሬታቸውን በግል ቅሬታቸውን ማቅረብ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ውጤቱ በኢንተርኔት የተለቀቀው ማንኛውም ቅሬታ ያለው አካል አይቶ ቅሬታውን ማቅረብ እንዲችል ነው የሚሉት አቶ አርአያ የመጨረሻ የሚሆነው በወረቀት ታትሞ የሚሰጠው ውጤት መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ቅሬታውን በአካል፣ በስልክ ካልሆነም በድርጅቱ ድረገፅ ላይ ማቅረብ እንደሚቻል ገልፀው ቅሬታ አቅራቢው የፈተና መለያ ቁጥሩን፣ ትምህርት አይነቱን አሟልተው ጥያቄ ቢያቀርቡ ከሰርትፍኬት ሕትመት በፊት ይስተናገዳሉ ብለዋል።