የእንግሊዝኛ ፈተና ጀርመናዊ ተማሪዎችን አስቆጣ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ከ30ሺ በላይ የጀርመን ተማሪዎች ከሰሞኑ የወሰዱትን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፈተና በመቃወም የበይነ መረብ የተቃውሞ ዘመቻ ጀምረዋል።
ቤደን ዌርትምበርግ በተሰኘችው የጀርመን ግዛት የትምህርት ሚኒስቴር በተዘጋጀው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ውስጥ የሚገኙ ጥያቄዎች 'ፍትሃዊ ያልሆኑ' እና ያረጁ ያፈጁ ቃላት የታጨቁባቸው ናቸው ሲሉ ተፈታኞች አማረዋል።
ለግዛቷ ባለስልጣናት ባስገቡት አቤቱታ ተማሪዎች ፈተናው ፍትሃዊ አለመሆኑ እንዲሁም አስቸጋሪነቱ ጠቅሰው በእርማት ወቅት ግምት ውስጥ እንዲገባ አሳስበዋል። የዘንድሮ ፈተና ከቀደምቶቹ ጋር ሊወዳደርም 'አይገባም 'ሲሉ ተሟግተዋል።
የግዛቷ ባለስልጣናት በበኩላቸው የተካተቱት ጥያቄዎች 'አግባብ ያላቸው ናቸው' በማለት ፈተና አውጪውን አካል ደግፈዋል።
በዘንድሮው ፈተና ተፈታኞች የእንግሊዝን ከአውሮፓ ህብረት መውጣት መሰረት ያደረጉ የካርቱን ስዕሎችን እንዲያነፃፅሩ እንዲሁም ሄነሪ ሮስ በ1934 እኤአ ከፃፉት መፅሃፍ ላይ የተመሰረቱ ጥያቄዎችን እንዲመልሱ ተጠይቀዋል።
ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ በሌላኛው የጀርመን ግዛት ሰሜን ራይን ዌስትፋሊያ ውስጥ የተፈተኑ ተማሪዎች በእንግሊዝኛ ፈተና ላይ ቅሬታ አቅርበው በድጋሚ እንዲከለስ ተደርጓል።








