ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"እናቴ የሞተችው ኤች አይ ቪ እንዳለብኝ ሳትነግረኝ ነው"
አንዳንድ ወላጆች በደማቸው ውስጥ ኤች አይ ቪ መኖሩን ለማንም ትንፍሽ ሳይሉ ወደ መቃብር ይወርዳሉ። ልጆቻቸው ጤና ሲያጡ እያዩ እንኳ ሚስጥራቸውን እንደያዙ እስከወዲያኛው ያሸልባሉ።
ብሪያን ኦሞንዲ ሲወለድ ቫይረሱ በደሙ ይገኝ ነበር። ከ10 ዓመቱ ጀምሮ የፀረ ኤች አይ ቪ መድሀኒት ይወስድ ነበር።
ነገር ግን 14 ዓመት እስኪሞላውና እናቱ እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ መድሀኒቱን ለምን እንደሚወስድ አያውቅም ነበር።
አሁን የ22 ዓመት ወጣት የሆነው ብሪያን "ትውልድ ይዳን፤ በኛ ይብቃ" እያለ በቤተክርስቲያናት አካባቢ ያስተምራል።
"ልጅ እያለሁ ታማሚ እንደነበርኩ ትዝ ይለኛል" የሚለው ብራያን "እየባሰብኝ ሲሄድና ሁኔታዬ ዕለት በዕለት ከመሻሻል ይልቅ እየከፋ ሲሄድ እናቴ ሆስፒታል ወሰደችኝ" ይላል።
ምርመራ ከተደረገለት በኋላ ኤች አይ ቪ በደሙ ውስጥ ስለተገኘ የፀረ ኤች አይ ቪ መድሀኒት መውሰድ ቢጀምርም እናቱ ግን የሚወስደውን መድሀኒት ለምን እንደሚውጥ ትንፍሽ አላለችም።
እናቱ ስትሞት አክስቱ ጋር ሄዶ መኖር ጀመረ። ያኔ የአክስቱ ጎረቤቶች ስለ ህመሙ መንሾካሾክ ጀመሩ። ልጆቻቸውም ይጠቋቆሙበት ነበር።
"ወላጆች ኤች አይቪ ካለበት ልጅ ጋር ልጆቻቸው እንዲጫወቱ አይፈቅዱም" ይላል።
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ ያገኛት አንዲት ሴት "ኤች አይ ቪ አለብህ አይደል" እንዳለችው በማስታወስ ስሜቱ እንዴት እንደተሰባበረ ይናገራል።
በኬንያና በሌሎች የአፍሪካ አገራትም ህፃናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በኤች አይ ቪ ይያዛሉ። ቫይረሱ በደማቸው እያለ የሚወለዱ ህፃናት ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩ ሳያውቁ ሕይወታቸውን ይገፋሉ።
አንዳንዶቹ መድሀኒት ተደብቀው እንደሚወስዱ የሚናገረው ብሪያን፤ "ማታ ማታ ሰው መተኛቱን፣ ጭር ማለቱን አይቼ ነበር መድሀኒት የምውጠው" ይላል።
የ27 ዓመቷ ዊኒ ኦሮንዲ በ12 ዓመቷ ኤች አይ ቪ በደሟ እንዳለ ስታውቅ በድንጋጤ ፊቷ ጭው ብሎ እንደነበር ትናገራለች።
"እናቴ ከሞተች ከሁለት ወራት በኋላ ታላቅ እህቴን ዶክተሩ ጠርቷት ሆስፒታል ብቻዬን እንድመጣና ምርመራ እንዳደርግ ጠየቃት" ትላለች።
ሐኪሙ እናቷ በኤድስ ምክንያት እንደሞተች ስለሚያውቅ እሷንም ኤች አይ ቪ መመርመር ፈልጓል።
እናም በምርመራው ቫይረሱ በደሟ ተገኘ።
ለቤታቸው ትንሿ ልጅ እሷ ናት፤ እህትና ወንድሞቿ ከቫይረሱ ነፃ ናቸው።
"ለምን እኔ? ከአራታችን መካከል እኔ ብቻ እንዴት ኤች አይ ቪ ሊገኝብኝ ቻለ? የሚለው ሀሳብ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ጎድቶኛል"
ለበርካታ ጊዜ መድሀኒቱን ለመጀመር አሻፈረኝ ብላ ቆየች። ነገር ግን በተደጋጋሚ እየታመመች የሆስፒታል አልጋ ስታዘወትር፤ ሐኪሟ ለትምህርት ቤቷ ርዕሰ መምህር ከትምህርት ቤት ለምን በተደጋጋሚ እንደምትቀር ለማስረዳት በሚል ያለችበትን የጤና ሁኔታ አስረዳ።
ርዕሰ መምህሩ ለሌላ መምህር፣ ከዛም ሁሉም የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ ኤች አይ ቪ እንዳለባት ሰማ።
ከዚህ በኋላ ሕይወቷ እንደነበረው አልቀጠለም። መገለል ይደርስባት ጀመር።
"በጣም አዘንኩ፤ ውጤቴን ለራሴ ቢነግሩኝ ምን ነበረበት? ራሴን ማጥፋት ፈለግሁ፤ ነገር ግን ራሴን ካጠፋሁ እህቶቼ እንደሚጎዱ ሳስብ ሀሳቤን ጠላሁት"
በኬንያ ፀረ ኤች አይ ቪ ዘመቻዎች የሚያደርጉ ቡድኖች የሥርዓተ ፆታና የሥነ ወሲብ ትምህርቶች እንዲያስተምሩ ይፈልጋሉ።
ዶ/ር ግሪፊንስ ማንጉሮ፤ የህፃናት አሳዳጊዎችና ወላጆች ልጆቻቸው ከዘጠኝ እስከ 11 ዓመት ሲሆኑ ስለ ኤች አይ ቪ ውጤታቸው እንዲነግሯቸውና ግልፅ ውይይት እያካሄዱ እንዲያሳድጓቸው ይመክራሉ።
"ልጁ ስለ ኤች አይ ቪ ምንነት መረዳት ሲችል ኤች አይ ቪ እንዳለበት በመንገር መድሀኒቱን እንዲወስድ ማድረግ ይቻላል" በማለት ህፃናቱን ያለምንም መረጃ መተው መድሀኒቱን እንዳይወስዱ ሊያደርግ እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።
ብሪያን፤ እናቱ የኤች አይ ቪ ውጤቱን ስላልነገረችው አይኮንናትም።
"ልትነግረኝ ትችል ነበር፤ ያልነገረችኝ ልትከላከለኝ ፈልጋ ይሆናል፤ ስለዚህ አልወቅሳትም"