ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአማራ ክልል በተከሰቱ ግጭቶች 224 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
በአማራ ክልል የተለያዩ ስፍራዎች ከተከሰቱ ግጭቶችን ጋር በተያያዘ 224 ሰዎች በቁጥጥር መዋላቸውን የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስታወቀ።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ምግባሩ ከበደ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በክልሉ የሕግ የበላይነትን የማስከበር ጉዳይ ትልቁ የፖለቲካም የመልካም አስተዳደር ሥራ ነው ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ግጭት በተፈጸመባቸው 3 አካባቢዎች ጥፋት የፈጸሙ ሰዎችን ለሕግ ለማቅረብ የምርመራ ሥራ ተጀምሯል ብለዋል። አቃቤ ሕጉ በማዕከላዊ እና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ኦሮሞ ማህበረሰብ አስተዳደር እና ከቤኔሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ ቦታዎች የምርመራ ሥራ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የፌደራል ፖሊስ፣ የክልል ፖሊስ፣ የፌደራል እና የክልሉ አቃቤ ሕግ እንዲሁም የዞን ፖሊስ የተካተቱበት የምርመራ ቡድን መመሥረቱንም አቃቤ ሕጉ ተናግረዋል። በማዕከላዊ እና ምእራብ ጎንደር ዞኖች 150 ሰዎች ጉዳያቸው እየተመረመረ በማረሚያ ቤት እንደሚገኙ አቶ ምግባሩ አስታውቀዋል።
ሆኖም ተጠርጣሪዎች ገና በቁጥጥር ሥራ ያልዋሉ ሲሆን ይህም ከነበረው ግጭት ስፋትና ውስብስብነት የተነሳ መሆኑን ጠቁመዋል።
በኦሮሞ ማህበረሰብ አስተዳደር እና በሰሜን ሸዋ ዞን ደግሞ ላለፉት ሶስት ወራት በተሰራው የምርመራ ሥራ ማስረጃ የተገኘባቸው 50 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አቃቤ ሕጉ ተናግረዋል።
በቤኔሻንጉል ጉሙዝ እና በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት 24 ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እየተከታተሉ ነው። "የአማራ ክልል በቅርቡ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት እና ሠላም የሰፈነበት ክልል ማድረግ እንደምንችል አምነን እየሠራን ነው የምንገኘው" የሚሉት አቃቤ ሕጉ ምግባሩ ከበደ፤ ህበረተሰቡ ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን ሳልፎ በመስጠት ሊተባበር ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።