ስለ ግንቦት 27/1983ቱ የበቅሎ ቤት የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት ፍንዳታ ምን ያስታውሳሉ?

ከደርግ መውደቅ አንድ ሳምንት በኋላ አዲስ አበባን ለሰዓታት በዘለቀ ከባድ ፍንዳታ ያናወጠው የበቅሎ ቤቱ የጦር መሣሪያ ማከማቻ ግምጃ ቤት ቃጠሎ ካጋጠመ ዛሬ ግንቦት 27/2013 ዓ.ም 30 ዓመት ሆነው።

ኢህአዴግ አዲስ አበባን ተቆጣጥሮ የአገሪቱ አስተዳዳሪ በሆነ በሳምንት ውስጥ የተከሰተው የዚህ ከባድ አደጋ መንስኤን በተመለከተ የተለያዩ ምክንያቶች የቀረቡ ሲሆን እስካሁን ይህ ነው ተብሎ በይፋ የቀረበ ምክንያት የለም።

ግንቦት 27/1983 ዓ.ም.፤ ደርግ ወድቆ ጊዜያዊ አስተዳደር ሥልጣን ከያዘ አንድ ሳምንት ሞልቶታል። አዲስ አበባ ከጥይት እና መሰል ድምፆች ጋብ ብላ በእርጋት ማሰብ የጀመረችበት ወቅት ነበር።

ነገር ግን ሌሊት 10 ገደማ የሆነውን ማንም አልጠበቀውም። አገር ሰላም ብለው እንቅልፍ ላይ ያሉ አዲስ አበባውያንን ቀልብ የገፈፈ ክስተት ተከሰተ። ከ100 በላይ ሰዎችን የቀጠፈ ጉድ።

ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በዕለቱ ያወጣው ዕትም ላይ የአዲስ አበባ ሕዝብ ቁጥር በግምት 3 ሚሊዮን ይሆናል ይላል። ታድያ ይህን ሁሉ ሰው በአንዴ 'ክው' የሚያደርግ ምን ሊሆን ይችላል?

የተሰማው ፍንዳታ ነበር። ከበ...ድ ያለ ፍንዳታ። ከጎተራ እስከ ሰሜን ሆቴል የተሰማ። ከአቃቂ እስከ ኮተቤ ቀልብን የገፈፈ።

መታሰቢያ ሸዋዬ ይልማ የዚያን ጊዜ የ12 ዓመት ታዳጊ ነበርኩ ትላለች፤ የ7ኛ ክፍል ተማሪ። ቢሆንም ክስተቱን መቼም አትረሣውም።

"በዚያ ሰሞን ከሁለት ሳምንት ጀምሮ ትምህርት ተዘግቶ ነበር። ልክ 'ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም ከአገር ኮበለሉ' ተብሎ የተነገረ 'ለት [ግንቦት 13] ቤተሰቦቻችን ሰብስበው ወደ ቤት አስገቡን። ከዚያ በኋላ ትምህርት አልነበረም።

"አስጨናቂ ሳምንት ነበር። ልክ በሳምንቱ [ግንቦት 20] የኢህአዴግ ሠራዊት አዲስ አበባ ገባ። ከዚያ በኋላ የጥይት ድምፅ አልነበረም፤ ትንሽ ጋብ ብሎ ነበር።"

አዲስ አበባ ከዚያ በፊት በነበሩት ሳምንታት የጥይት ይሁን መሰል ፍንዳታዎች ድምፅ ይህን ያህል ብርቋ አልነበረም። መታሰቢያ ትቀጥላለች. . .

"ከእንቅልፋችን የቀሰቀሰን ፍንዳታው ነበር። መሬት 'ሚያንቀጠቅጥ ዓይነት ፍንዳታ ነበር። በዚያ ላይ ጨለማ ነው። ምን እንደሆነ አላወቅንም፤ እስከዛን 'ለት ከሰማናቸው ፍንዳታዎችም በጣም የተለየ ነበር።

"ሁሉም ሰው ተነሳ፤ ነገር ግን ግራ በገባው ስሜት ውስጥ ነበር። ጦርነት ነው እንዳንል ጦርነቱ አልቋል. . .ምን እንበለው? አየቆየ ሲመጣ የጥይት የሚመስሉ ትንንሽ ፍንዳታዎች መስማት ጀመርን።"

ፍንዳታውን የሸሹ ሰዎች እግራቸው ወደመራቸው በአራቱም የከተማዋ አቅጣጫ መትመም ያዙ። ወደ እነመታሰቢያ ሠፈርም የመጡ አልጠፉም።

"እንግዲህ አስበው ሠፈራችን ሰሜና ማዘጋጃ ነው። ግን ፍንዳታውን የሸሹ ሰዎች በግምት ከፍንዳታው አንድ ሁለት ሰዓት በኋላ እኛ ሠፈር ደርሰዋል። ወላጆቼ ወጥተው ሲጠይቁ ፍንዳታ እንደሆነ ተረዱ። የሚቀጣጠል ነገር እንዳለም ከሰዎቹ ሰሙ።

"ወላጆቼም ግራ ገብቷቸው ነበር። እኛም እንውጣ ወይስ ትንሽ እንጠብቅ ዓይነት ነገር ነበር የነበረው። መጨረሻ ላይ አንድ ድብል...ቅ ያለ ፍንዳታ ተሰማ። በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ መስኮታችን ሁላ የሚረግፍ ነበር የመሰለው። ከዚያ በኋላ ነው ፍንዳታውም የተረጋጋው፤ ቀኑም እየነጋ መጣ።"

የጦር መሣሪያ ማከማቻ

ይድነቅ አብርሃ ክስተቱን ለመዘገብ ካሜራቸውን አንግበው ወደሥፍራው ካመሩ ሰዎች መካከል ነበር። ይድነቅ በወቅቱ የሚያነሳቸውን ፎቶዎችን እና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማሕደር ክፍል ያስረክባል። ቢሯቸው የነበረው ደግሞ አቡነ ጴጥሮስ አካባቢ የነበረው የኢትዮጵያ ራድዮ ዋና መሥሪያ ቤት።

"ፍንዳታውን ስንሰማ የኛ 'ክሩ' ቪዲዮ እና ፎቶግራፍ ለማንሳት ወደዚያ ሄደ። የፈነዳው የጦር መሣሪያ ማከማቻ የነበረ ሥፍራ ነበር፤ በርካታ ብረታ ብረቶችም ነበሩ ሥፍራው ላይ። ፍንዳታው አካባቢውን በጭስ እንዲዋጥ አድርጎ ነበር። ብዙ ተጎጅዎችም ነበሩ። በርካቶች ሞተዋል፤ የቆሰሉም የትየለሌ ነበሩ። እኛ ፎቶ እና ቪደዮ ስናነሳ የነበረው እዚያ የነበረውን ሁኔታ ነበር።"

ያኔ ጎተራ፤ እንደዛሬ በማሳለጫ ሳትከበብ ግዙፍ የነዳጅ ማከማቻ እና የለስላሳ ፋብሪካ ነበሩባት። የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መናኸሪያም ነበረች ጎተራ። "በጣም አስገራሚው ነገር እንዲያውም ነዳጅ ማደያው አለመፈንዳቱ ነው" ትላለች መታሰቢያ።

"ጎተራ፤ አሁን ያለውን ቅርፅ ሳይዝ በፊት 'ኮንፊውዥን ስኩዌር' ነበር የምንለው። መዓት አስፋልቶች የሚገናኙበት ነበር፤ ባቡሩም ያልፍ ነበር በዚያ በኩል።"

በሁለቱም አቅጣጫ ነዳጅ ማከማቻዎች ነበሩ፤ የእህል ጎተራው አለ፤ ለስላሳ ፋብሪካው አለ። ሰዉ በኋላ ላይ እንደ ተዓምር ያወራው 'ነዳጅ ማደያዎቹ አለመፈንዳታቸው' እያለ ነበር። ምክንያቱም አደጋ የበለጠ የከፋ ይሆን ነበር።

በወቅቱ በፍንዳታው ምክንያት ከ100 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተነገረ። የቆሰሉም በርካታ ነበሩ። ያኔ የነበረው ጊዜያዊ አስተዳደር ጣቱን በደርግ ሰዎች ላይ ቀሰረ። ማከማቸውን ሆን ብለው ያፈነዱት የደርግ 'ርዝራዦች' ናቸው አለ።

ምሽት ላይ ዜና ሲነበብ ከአደጋው ሌላ አስደንጋጭ ዜና ተሰማ፤ ታዋቂው ጋዜጠኛ ሞሐመድ አሚን በፍንዳታው ምክንያት አንድ እጁን ማጣቱ።

መድ አሚን

ይድነቅ ስለ ሞሐመድ የሚያስታውሰውን ሲወጋ "እኛ በሥፍራው ስንደርስ ሞሐመድ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ፎቶ እያነሱ ነበር" ይላል።

ሞሐመድ አሚን እጁ ላይ ጉዳት የደረሰበት በሁለተኛው ፍንዳታ ነው። ከዚያ በፊት ግን ፍንዳታውን እና አካባቢውን እየዞረ ሲቃኝ፤ ምስልም ሲወስድ ነበር። ነገር ግን ሁለተኛው ፍንዳታ የእርሱን ግራ እጅ የባልደረባው ጆን ማታይን ነብስ ሊወስድ ግድ ሆነ።

"እነዚህማ ለገንዘብ ብለው ነው እንጂ እንዴት እንዲህ ዓይነት ሥፍራ እየገቡ ፎቶ ያነሳሉ በማለት ራቅ ብለን የቆምነው እኔና የኛ ካሜራ ክሩ ስናወጋ ነበር" ይላል ይድነቅ የሞን ጀግንነት ሲያስታውስ።

"አደጋው ሲደርስ በሥፈራው የነበረው አምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ወሰዳቸው። በቦታው ግርግር ነበረ። ካሜራቸውን ጥለው ነበር የሄዱት። እኛ ነን ካሜራቸውን ሰብስበን ያስቀመጥንላቸው።"

የዚያን ጊዜ ታዳጊ የነበረችው ለመታሰቢያም ስለሞሐመድ የሰማችውን ታስታውሳለች "ቀልቤን ስቦት የነበረው ምሽት ላይ የተነገረው ዜና ነው። ሞሐማድ አሚን በፍንዳታው ምክንያት ጉዳት ደረሰበት ተብሎ ሲነገር። ሞሐመድ አሚን ለእኔ በጣም ትልቅ 'አይዶል' ብዬ የምለው ጋዜጠኛ፤ ከኢትዯጵያ ጋር ልዩ ቁርኝት ያለው ሰው ነው።"

ሞሐመድ አሚን አንድ እጁ ጉዳት ደርሶበት እንኳ በአንዱ እጁ ይቀርፅ ነበር አሉ። እውነት ይሆን? ማን ያውጋ የነበረ. . . እንዲሉ ይህን ጥያቄ ለይድነቅ ሰነዘርንለት።

«አይይይይይ. . .እውነት አይደለም። ብዙ ደም እየፈሰሰው ነበር እኮ። ኋላ ላይ በሕክምና ተቆረጠ አንጂ፤ አንድ እጁ ተንጠልጥሎ ነበር። 'ሬዚዝታንስም' አልነበረውም፤ ያ ሁሉ ደም እየፈሰሰ እንዴት ብሎ? ካሜራው እኮ ወድቋል። አምቡላንስ ለሕክምና ወሰደው፤ ንብረቱን ደግሞ እኛ ይዘንለት ሄድን። በኋላ ነው መጥቶ የተረከበው።"

ድኀረ-ኢሕአዴግ ትውልድ ስለ ጎተራው ፍንዳታ እምብዛም ትዝታ ላይኖረው ይችል ይሆናል። በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ሥፍራ ካለው ወርሃ ግንቦት ክስተቶች አንዱ መሆኑ ግን አልቀረም።

*ይህ ዘገባ ከሁለት ዓመት በፊት የተዘጋጀ ሲሆን ከጥቂት ማስተካከያ ጋር በድጋሚ የቀረበ ነው።