በኦሮሚያ ክልል ብክለት አስከትለዋል በተባሉ 22 ፋብሪካዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

የፎቶው ባለመብት, ALFREDO ESTRELLA
በዚህ አመት በኦሮሚያ ክልል የአፈር፣ የውሃና የአየር ብክለት አስከትለዋል በተባሉ 22 ፋብሪካዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ።
የክልሉ የተፈጥሮ ሃብት ደንና የአየር ንብረት ባለስልጣን አቶ ቦና ያዴሳ እርምጃ ከመውሰድ በተቃራኒ በዘርፉ በጎ አስተዋጽኦ ላበረከቱ 18 ፋብሪካዎች የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል ብለዋል።
እርምጃ የተወሰደባቸው ፋብሪካዎች አብዛኞቹ የቆዳ፣ የብረታብረት፣ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችና የቡና ማጠብ ስራ ላይ የተሰማሩ ናቸው ያሉን ኃላፊው ለጊዜው ፋብሪካዎቹ ስራቸውን አቁመው የቆሻሻ ማስወገድ ስርዓታቸው ላይ ማስተካከያ እስኪያደርጉ ተዘግተዋል ብለዋል።
ከእነዚህም መካከል 18 የሚሆኑት የሚጠበቅባቸውን ማስተካከያ አድርገው ወደ ስራ መግባታቸውን አቶ ቦና ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ሕዝቡ ቅሬታ የሚያሰማባቸው ፋብሪካዎች ላይ ጠንከር ያለ ክትትል እንደሚያደርጉ ኃላፊው ጨምረው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአለም አቀፍ ደረጃ ዛሬ እየተከበረ የሚገኘውን የአካባቢ ጥበቃ ቀን በማስመልከት ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የአየር ብክለት ተጽዕኖ የአየር ብክለት ተጋላጭነት እየጨመረ ነው ብለዋል።
በአለም አቀፍ ደረጃ ዛሬ የአካባቢ ጥበቃ ቀን "አየር ብክለትን" ዋና ጉዳዩ አድርጎ በቻይና እየተከበረ ይገኛል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ከአየር ብክለት ጋር በተያያዘ በሚከሰት የጤና ችግር ምክንያት በአለም 7 ሚሊዮን ሰዎች ያለ እድሜያቸው እንደሚሞቱ ያትታል።
ከእነዚህ መካከል 4 ሚሊዮን የሚሆኑት በእስያ ፓስፊክ የሚገኙ ናቸው። ኢትዮጵያ በአየር ብክለት ከሌሎች ሃገራት ጋር ስትነጻጸር የተሻለች ብትሆንም በትልልቅ ከተሞችና በከተሞች አቅራቢያ ከፋብሪካዎች መስፋፋትና ከተሽከርካሪዎች ብዛት ጋር በተያያዘ የአየር ብክለት እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሷል።
ፕሮፌሰር ፍቃዱ ከአየር ብክለት የሚያስከትለው ጉዳትና ህብረተሰቡ ሊያደረግ በሚገባው ጥንቃቄ ላይ መሥሪያ ቤታቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ላይ አትኩሮ እየሰራ መሆኑን ነግረውናል።
ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ቀንን በመጭው ቅዳሜ በአዳማ ስታከብር ዋናው ትኩረት በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ መፍጠር እንደሆነም ጨምረው አስረድተዋል።
በአየር ብክለት ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች መካከል የሳምባ በፍጥነት ማርጀት፤ አስም፤ ብሮንካይት፤ ካንሰር ይገኙበታል።
- ከአለም ህዝብ 92% የሚሆነው የተበከለ አየር እየተነፈሰ ይኖራል።
- በአየር ብክለት ምክንያት የሚፈጠሩ የጤና እክሎችን ለማከም ከዓለም ኢኮኖሚ በአመት 5 ትሪሊዮን ይወጣል።
- በኦዞን ብክለት ምክንያት በ2030 የሰብል ምርት በ26% ሊያንስ ይችላል ተብሎ ይገመታል።
















