ኢንዶኔዢያ፡ የመስጠም አደጋ የተጋረጠባት ዋና ከተማ ልትቀየር ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢንዶኔዢያዋ ዋና ከተማ ጃካርታ በዓለማችን እጀግ አስፈሪ በተባለ ፍጥነት እየሰመጠች ስለሆነ በሌላ ከተማ ልትቀየር እንደሆነ የሀገሪቱ የእቅድ ሚኒስትር መስሪያ ቤት አስታውቋል።
ሚኒስትሩ ባምባንግ በሮጆንጎሮ እንደገለጹት ውሳኔው እጅግ በጣም ወሳኝ ሲሆን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆኮ ዊዶዶ የትኛዋ ከተማ ጃካርታን እንደምትተካ መርጠዋል ሲሉ ውሳኔውን ይፋ አድርገዋል።
አዲሱ ዋና ከተማ የት ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነገር ባይኖርም ብዙዎች ግን ፓላግካራያ የተባለችው ከተማ መሆኗ አይቀሬ ነው እያሉ ነው።
ከ10 ሚሊየን በላይ ነዋሪዎች ያሏት ጃካርታ በፍጥነት ወደ ምድር እየሰጠመች መሆኑ የኢንዶኔዢያ ባለስልጣናትን አሳስቧቸዋል። በቅርቡ የሃገሪቱን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያሸነፉት ፕሬዝዳንት ዊዶዶ ደግሞ ይህንን ጉዳይ ቅድሚያ የምሰጠው ኃላፊነቴ ነው ብለዋል።
ምንም እንኳን ኢንዶኔዢያውያን በአውሮፓውያኑ 1945 ከኔዘርላንድስ ነጻነታቸውን ካገኙ ጀምሮ ዋና ከተማዋ ጃካርታን በሌላ ለመቀየር ቢያስቡም እስካሁን አልተሳካላቸውም ነበር።
በቅርቡ በተሰራ አንድ ዓለማቀፍ ጥናት መሰረት ጃካርታ በዓለማችን እጅግ ከተጨናነቁ ከተሞች መካከል አንዷ ነች። የመንግስት ባለስልጣናትም ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ በከፍተኛ የፖሊስ ኃይል ታጅበው ለመሄድ ይገደዳሉ።
በዚህም መጨናነቅ ምክንያት በየዓመቱ 6.8 ቢሊየን ዶላር ሃገሪቱ እንደምታጣ የሀገሪቱ የእቅድ ሚኒስትር መስሪያ ቤት አስታውቋል።
የጃካርታን ሥነ ምድራዊ አቀማመጥ የሚያጠኑ ተመራማሪዎች እንደገለጹት ከተማዋ በአውሮፓውያኑ 2050 ሙሉ በሙሉ የምትሰጥም ሲሆን ባለፉት 10 ዓመታት ብቻ 2.5 ሜትር ወደታች ሰጥማለች።
ይህ ማለት ደግሞ ከተማዋ በየዓመቱ ከ1 እስከ 15 ሴንቲሜትር ወደታች ትገባለች ማለት ነው።
ዋና ከተማው ከጃካርታ ወደሌላ ቦታ ከመቀየሩ ጋር በተያያዘ ፕሬዝዳንት ጆኮ ዊዶዶ ሶስት አማራⶐች ቀርበውላቸው ነበር ተብሏል። የመጀመሪያው እዛው ጃካርታ ውስጥ አዲስና ልዩ ክልል በመመስረት የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ወደ እዛው ማዘዋወር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሌላ ተተኪ ከተማ ማፈላለግ ነው።
የመጨረሻውና ፕሬዝዳንቱ የመረጡት ሃሳብ ሳይሆን አይቀርም የተባለው ደግሞ አዲስ ከተማ ሌላ ቦታ ገንብቶ ዋና ከተማውን መቀየር የሚለው ነው።












