የአውሮፕላን አደጋዎች የበዙበት 2018

አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, PA

በባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በአውሮፕላን አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ2017 ጋር ሲወዳደር ከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ቢያሳይም፤ የአውሮፕላን ጉዞ ዝቅተኛ አደጋ ከሚያጋጥማቸው የመጓጓዣ ዘዴዎች መካከል ዘጠነኛው ነው ተብሏል።

በ2017 ከአውሮፕላን አደጋዎች ጋር በተያያዘ 44 ሰዎች ብቻ የሞቱ ሲሆን፤ ባሳለፍነው 2018 ግን 556 ሰዎች በአውሮፕላን አደጋ ህይታቸውን አጥተዋል።

ከሁሉም የከፋው የተባለለት አደጋ ደግሞ የኢንዶኔዢያው አየር መንገድ አውሮፕላን ተከስክሶ 189 ሰዎች የመሞቱበት ነው ተብሏል።

በአንጻሩ 2017 በአውሮፕላን አደጋዎች በታሪክ ትንሽ ሞት የተመዘገበበት ሆኖ ነበር ያለፈው።

የኔዘርላንዱ 'ኤኤስኤን' የተባለው ድርጅት እንዳስታወቀው ባሳለፍነው ዓመት የብዙ ሰዎችን ህይወት የቀጠፉ 18 የአውሮፕላን አደጋዎች ተከስተዋል።

ከእነዚህም መካከል ደግሞ 189 ሰዎች ህይወታቸው ያለፈበት የኢንዶኔዢያው ቦይንግ 737 አደጋ፣ 112 ሰዎች የሞቱበት የኩባው አውሮፕላን አደጋ፣ በኢራን ዛግሮስ ተራሮች ላይ ተከስክሶ 66 ሰዎች የሞቱበት አደጋ እንዲሁም የ51 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው የኔፓሉ አየር መንገድ አደጋ ይጠቀሳሉ።

ምንም እንኳን የዓለም አቀፍ ኤቪዬሽን ድርጅቶች ከባለፉት ሃያ ዓመታት ጀምሮ አደጋዎችን ለመቆጣጠር እየሰራን ነው ቢሉም፤ የሟቾች ቁጥር ግን እምብዛም መቀነስ እያሳየ አይደለም።