መከፋፈል ያጠላበት ጉዞ አድዋ

ጉዞ አደዋ

የፎቶው ባለመብት, Yared Shumete

የአድዋ ድልን ከድንበር ሉዓላዊነት ጋር አያይዞ መተንተን የተለመደ ከመሆኑ አንጻር ድሉ አነሰ በዛ የሚለው ጭቅጭቅ ከዚህ መሰረት እንደሚፈልቅ በዕውቀቱ ስዩም ሐተታ አድዋ በሚለው ፅሁፉ ያትታል።

ነገር ግን ይላል በዕውቀቱ "በኔ ግምት የአድዋ ድል ትልቅ ጭብጥ "የሰውነት ክብር" ይሰኛል። ቀደምቶቻችን ወደ አድዋ የጋለቡት በግፍ የተነጠቁትን የሰውነት መታወቂያ ለማስመለስ ነው። እንዲያውም ሰው መሆናቸውን በማያዳግም መንገድ ያረጋገጡት አድዋ ላይ ነው ማለት ይቻላል" አክሎም ወገኖቼ ሰው መሆንን ማረጋገጥ ቀላል ነገር አይምሰላችሁ" ይላል።

የቅኝ ግዛትን አሻፈረኝ ያሉ ቀደምቶችን በሚዘክረው በዚህ ፅሁፉ "በውርደት ከመኖር በክብር መሞት ይሻላል" የሚለውንም መርጠው ከሰው በታች ሊያደርጋቸው የመጣውን ቅኝ ግዛት እንዴት አድርገው ድል እንደነሱትም ዘክሯል።

ለዘመናት ያህል "የጥቁር ነፃነት ተምሳሌት"፤ የዓለም ድሃ ሀገሮችን የናቀና ጦር መሳሪያውን የተማመነ ኃይል የተንበረከከበት በሚልም ሲዘከር ቢኖርም፤ የአድዋ ታሪካዊ አተረጓጎም አንዳንድ ሀሳባዊ ፍጭቶችንም ያስተናግዳል።

በአሁኑም ሰዓት አፄ ሚኒልክ የነበራቸው ሚና፣ የሰንደቅ አላማ ጉዳይ በታሪክ ተርጓሚዎች ዘንድ መነታረኪያ ሆኗል።

በዚህ አመት ደግሞ ሀገሪቱ ካለችበት የተለያዪ የብሔር ግጭትና ስጋት ጋር ተያይዞ ለአምስት አመታት ሲካሄድ የነበረው አድዋን የሚዘክረው ጉዞ አድዋ አወዛጋቢ ሁኔታን ፈጥሯል።

ጉዞው ከመካሄዱ በፊት በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ዘመቻዎች የተከፈቱ ሲሆን፤ ይህም የሰንደቅ አላማው ልሙጥ መሆን፣ የሚሰሙ መፈክሮች፣ "ሁለቱን ትግርኛ ተናጋሪዎች ህዝቦች እንዲከፋፈሉ ያደረገውን ዕለት ማክበር" እንዲሁም ቀጥታ የጉዞውን አስተባባሪዎች "ፀረ-ትግራይ" ናቸው በሚል ወደ ትግራይ ክልል እንዳይመጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።

የዚህንም አመት የጉዞ አድዋ ለየት የሚያደርገው በእንደዚህ አይነት በተከፋፈለ ስሜት መደረጉ መሆኑን የጉዞው አንደኛው አስተባባሪ ያሬድ ሹመቴ ይናገራል።

"በጣልያን ወረራ ወቅት ትልቁ ዘመቻ ወራሪውን ጦር ከኢትዮጵያ ለማስወጣት ነበር። አሁን ደግሞ የተወረርነው በሌላ የውጭ ጦር ሳይሆን በራሳችን አመለካከት ውስጥ ባለው የአንድነት ስሜት መደብዘዝ፣ የኢትዮጵያዊነት ሀሳብ ጥርጣሬ ውስጥ በወደቀበት ወቅት መሆኑ ነው።" ይላል።

ከወትሮው በተለየ መልኩ ከአዲስ አበባ ሳይሆን ከሐረር የተነሳው ጉዞ አድዋ ተሳታፊዎችን ከመላው ኢትዮጵያ ማሳተፉ ህዝቡን በአንድ ቦታ፣ ስሜትና ሀሳብ የሚያሰባስብ ኃይል እንደሆነም ያምናል።

እንዲህ አይነት ዘመቻ መከፈቱ አዲስ እንደሆነ የሚናገረው ያሬድ ጉዳዩ በሀገሪቱ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ዕውነታ ነፀብራቅ ስለሆነ፤ ግራ ቀኙን መፈተሽ እንደሚያስፈልግ ይናገራል።

ባለው የሃገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የሀሳብ መሪዎች የህዝቡን ስሜት የሚያስተጋቡ አክቲቭስቶች ትኩረት መስጠትና ሌሎች ችግሮችን አንስተው በይበልጥ ድምፃቸውን ለማሰማት እንደሞከሩ ያምናል።

ጉዞ አደዋ

የፎቶው ባለመብት, Yared Shumete

ይህንን በሁለት መልኩ የሚያየው ያሬድ በአሉታዊ ብቻ ሳይሆን በአዎንታዊ ጎኑ መታየት እንዳለበት ያምናል። በአንደኛው በኩል የሚያነሳው በአሁኑ ሰዓት ሀገሪቷ ላይ ያልተመለሱ ጥያቄዎችና ብዙዎችን እያስጨነቀ ያለው በአንድነት፣ በህብረትና በፍቅር የመኖር ጥያቄ አደጋ ውስጥ በወደቀበት ሰዓት፤ ሀሳቦች የተንፀባረቁበት መድረክ የአድዋ ጉዞ መሆኑ፣ እንዴት ትኩረት እንዳገኛና በበጎነት መታየት እንዳለበት ገልጿል።

" መንግሥትም ራሱ በዋናነት በዚህ በፌደራሊዝም ስርአት ውስጥ ከትግራይ ክልልና ከትግራይ ነዋሪ ህዝብ ባለው ግንኙነትና መስተጋብር ውስጥ እንዲህ ደመቅ ብሎ የተለያዩ አሉታዊ ተፅእኖ መፍጠር የሚችሉ ቅስቀሳዎች መደረጉ የስሜቱ ነፀብራቅ በመሆኑ ምክንያት፤ ይህንን ቆም ብሎ ሁሉም አካል ማየት እንዲችል ለምንድን ነው አብዛኛው ሰው ላይ ጥርጣሬ ያደረው የሚለውን እንዲፈተሽ እድል የሚሰጥ ነው" ይላል።

በተቻለ መጠን የመፍትሄው አካል ለመሆን እንደሚፈልጉ የሚናገረው ያሬድ በተቻለ መጠን መሰዳደብና እልህ ውስጥ ከመገባባት ይልቅ "የፍቅርን ኃያልነትና ታጋሽነት" ማሳየት እንደሚያስፈልግም ይገልጻል።

"ዘመቻውን የከፈቱት ሰዎች የተናገሩበት ምክንያት ሊኖራቸው ይችላል። ማጥናት እና ለዚህ መልስ እንዲሰጥ በሁሉም በኩል ግፊት ማድረግ አለብን ብየ አስባለሁ። ስለዚህ የመግፋትም የመሳብም ሀሳብ ውስጥ በየትኛው በኩል ምን አይነት ሚና ነበር የሚለውን እያየን ካልሄድን ምንም ለውጥ አያመጣም። "ይላል

የትግራይን ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ህዝብ ነው የሚለው ያሬድ በባለፉት አምስት አመታትም የነበረውንም መስተንግዶ እንደ ምሳሌ ያነሳል።

"በፍቅር በተለየ ትህትና እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በጨዋነት ሲያስተናግደን እንደዚሁ አልጋውን እየለቀቀ ሲያሳድረን ያለውን መሶቡን ገልብጦ እያበላ ሲቀበለን የነበረ ህዝብ ነው። በኛ ላይ ችግር አለው ብለን በጭራሽ አናምንም።" ይላል።

በአንዳንድ ዘመቻዎች ላይ ማስፈራሪያ ቢሰጣቸውም፤ እነ ያሬድ ግን በጭራሽ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ።

ጥበቃን ወይም የህግ ከለላን ማግኘት መፍትሔ አይደለም የሚለው ያሬድ፤ የግላቸውን ሳይሆን ሀገሪቷ ላይ ያጠላውን ስጋት በቀረፈ መልኩ ችግር እንደሌለ አሳይተው የበለጠ መተማመን በኢትዮጵያ ውስጥ መፍጠር ዋነኛ አላማቸው ነው።

"እኛ አንድ ነገር ብንሆን በሀገር ላይ የሚያመጣው መጥፎ ጥላ ስላለ ይህንን አንመኘውም፤ ባዶ መስዋእትነት የሚከፈልበት ጉዳይ አይደለም" የሚለው ያሬድ ምንም አይነት ጥበቃ ሳይደረግላቸውና የሀገር ስሜት ሳይጠፋ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ መንቀሳቀስ ችግር አለመሆኑን በሚያሳይ ሁኔታ ማከናወን ይፈልጋል።

በዚህ ጉዞም ዋነኛ ማሳካት የሚፈልጉት በጎ የሆኑ ህዝባዊ ስሜቶች የሚተላለፉበት መድረክን ለመፍጠ ነው።

በማህበራዊ ሚዲያ የሚነገሩ ነገሮች ተሰሚነታቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ እየደረሰ ከመሆኑ አንፃር በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ብቻ የቀረ ነው ብሎ እንደማያምንና ከእውነታው የራቀ ነው የሚል ሽፋን ተሰጥቶ ሊድበሰበስ አይገባም ይላል።

ነገር ግን ከትግራይ ክልል ብዙ ነዋሪዎች የሚደውሉላቸው ሲሆን በባለፉት አምስት አመታት እንደደገፏቸው አሁንም እንደሚደግፏቸውና፤ አይዟችሁ አትስጉ ምንም አዲስ ነገር የለም የሚሉ ሲሆኑ ይህም ለያሬድ ተስፋ ሰጭ ነው።

"ይህ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያለው መሬት ላይ ካለው የተለየ ነው። ይህም ጉልበት የሚሰጥና የሚያነሳሳ ነው።'' ብሏል።

የሚደውሉላቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆን ከፌዴራል መንግሥት በኩል ድጋፍ እንዲሁም ፍቃድ ተሰጥቷቸዋል። ለየክልሎቹም የድጋፍ ደብዳቤ ተጽፎላቸዋል።

የተለያዩ የክልል መሪዎች የሚያስተዳድሩትን አካባቢ ደህንነት በማረጋገጥ በተለያዩ አካባቢዎች መንቀሳቀስ ስጋት የለውም በሚል አጋርነታቸውን ያሳያሉ እንዲሁም ኑልን ይላሉ ብሎ ቢያስብም፤ ባይጠሯቸው እንኳን መሄዳቸው እንደማይቀር ይናገራል።

"መሄዳችን አይቀርም በግድና በእልህ ሳይሆን በፍቅር እያሸነፍን እስከ መጨረሻው ድረስ እንደርሳለን። ይህንን ካደረግን አድዋ ኢትዮጵያውያንን አንድ ለማድረግ በድጋሚ ምሰሶ ይሆናል" ይላል።

የታሪክን አረዳድ በሚመለከት የተለያየ ትንታኔ የሚሰጥበት ከመሆኑ አንፃር፤ በታሪክ ላይ ያለው ግንዛቤ መለያየቱ የፖለቲካው ጫና ውጤት ነው ብሎ የሚያምነው ያሬድ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ ማስታረቅ፣ ማስተካከል እንደሚያስፈልገውና ይህም እስከ ትምህርት ስርአቱ ድረስ ሊዘልቅ እንደሚገባ በአፅንኦት ይናገራል።

በአጠቃላይ 35 ሰዎች በሚሳተፉበት ይህ ጉዞ መነሻውን ሐረር ያደረገ ሲሆን፤ 1540 ኪሎ ሜትር ርቀትን ይሸፍናል። ሁለት ወር ከአንድ ቀን በሚፈጀውም ጉዞ የኢትዮጵያን ስምና ለሀገሪቷ አንድነት፣ ህብረት፣ ፍቅር የሰሩ ጀግኖች እንደሚዘከሩ ያሬድ ይናገራል።