መምህራን የበለጠ ክብር የሚያገኙት የት ሀገር ነው?

የፎቶው ባለመብት, ZACHARIAS ABUBEKER
መምህራን በተማሪዎቻቸው ዘንድ መከበርን ከፈለጉ ቻይና፣ ማሌዢያ ወይም ታይዋን ቢያስተምሩ ይበጃቸዋል። ምክንያቱም አንድ ዓለም ዓቀፍ ጥናት እንደሚያሳየው በእነዚህ ሶስት ሀገራ የሚማሩ ተማሪዎች ናቸው ለመምህራን ክብር ያላቸው።
በተገላቢጦሽ በብራዚል፣ እስራኤልና ጣሊያን መምህራን ከተማሪዎቻቸው ክብርን ለማግኘት እንኳ ቢናፍቁ ምኞታቸውን ውሃ ይበላዋል እንጂ አያገኟትም።
እንግሊዝ ከአሜሪካ ከፈረንሳይና ከጀርመን ተሽላ በደረጃ ከተቀመጡት 35 ሀገራት ዝርዝር ውስጥ መካተት ችላለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ተማሪዎች ለመምህራኖቻቸው ያላቸው ክብርን በተመለከተ ከተጠየቁ 35 ሺህ ሰዎች መካከል በርካቶች ከሁሉም አናት ላይ ቁጭ ያደረጓት ቻይና ናት።
በአውሮጳና በደቡብ አሜሪካ "በአጠቃላይ ተማሪዎች መምህራኖቻቸውን አያከብሩም የሚል አመለካከት አለ" ይሁን እንጂ ተማሪዎች ለመምህራኖቻቸው ያላቸው ክብር እንደ ደቡብ ኮሪያና ሲንጋፖር ባሉ የኤዢያ ሀገራት ጠንካራ ነው።
በእነዚህ ሀገራት የሚገኙ ተማሪዎችም ዓለም አቀፍ ፈተናዎች ላይ ሲቀመጡ ተፎካካሪዎቻቸውን ሲዘርሩ ነው የሚስተዋለው።
ጥናቱን ያካሄዱት ባለሙያዎችም እንዳሉት ለመምህርነት ክብር ባለበት ስፍራ ብቃቱ እና ተሰጥኦው ያላቸውን መምህራን በማምጣት የተማሪዎቹን ተወዳዳሪነት ከፍ ማድረግ እንደሚያስችል ያሳያል ብለዋል።
የመምህርነት ሙያን ተወዳጅ መሆኑን ለማሳየት ከተጠየቁት ጉዳዮች መካከል ወላጆች ለልጆቻቸው መምህርነትን እንደሙያ እንዲቀበሉት ይነግሯቸዋል ወይ የሚለው ነው።
በቻይና፣ ሕንድና ጋና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸው መምህር እንዲሆኑ ይነግሯቸዋል።
ወላጆች ለመምህራን ያላቸው አመለካከትም በጥናቱ ተካትቷል።
በጥናቱ ከተካተቱ ሀገራት መካከል በርካታ ወላጆች የመምህራን የስራ ሰዓትን ዝቅ አድርገው ይመለከታሉ። ይህ መምህራን ረጅም ሰዓት በሚሰሩበት ኒው ዚላንድም ሆነ ዝቅተኛ ሰዓት በሚሰሩበት ፓናማና ግብፅ ተመሳሳይ ነው።
በትምህርት ስርዓታቸው የላቁ በተባሉት ካናዳና ፊንላድ የሚገኙ መምህራን ትንሽ ሰዓት ቢሰሩም ወላጆች ግን ረጅም ሰዓት እንደሚሰሩ ያስባሉ።
መምህራን የሚከበሩባቸው ሃገራት በደረጃ
1. ቻይና
2. ማሊዢያ
3. ታይዋን
4. ሩሲያ
5. ኢንዶኔዢያ
6. ደቡብ ኮሪያ
7. ቱርክ
8. ህንድ
9. ኒውዚላንድ
10. ሲንጋፖር














