ኢትዮጵያ ካሏት ሚኒስትሮች ግማሾቹ ሴቶች እንዲሆኑ አደረገች

በትናንትናው የህዝብ እንደራሴዎች ውሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ የሚኒስትሮችን ሹመት ሲያፀድቁ ሴቶች ግማሽ ያህሉን ሹመቶች አግኝተዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር በአዲሱ ሹመት ቀዳሚው ተግባርዎት የሚሆነው ምንድን ነው የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።

እሳቸው በመጀመሪያ ቢሮው ውስጥ ያለውን ሁኔታ በሚገባ ማጥናት ውጤታማ ሥራ መስራት የሚያስችሉና በሌላ በኩል ደግሞ እንቅፋት የሚሆኑ ሁኔታዎችን በመለየት የአሰራር፣ የመመሪያና የፖሊሲ ለውጥ የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ካሉ ጥናት ላይ በመመስረት ለውጦችን አድርጎ ህብረተሰቡ ጥሩ የሚባል አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል።

እሳቸው በሚመሩት በዚህ ተቋም ውስጥ በቀጣይ በርካታ ሴቶች ወደ ሃላፊነት ይመጡ እንደሆ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ ብቃት ኖሯቸው ነገር ግን በተለያየ ምክንያት የሚገባቸውን ሃላፊነት የማያገኙ ሴቶች ስላሉ በርግጥም ወደ ሃላፊነት እንዲመጡ የተቻላቸውን እንደሚያደርጉ ነገር ግን ሴቶች ሴት በመሆናቸው ብቻ ሃላፊነት ቦታ ላይ እንደማይቀመጡ አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የነበሩትና አሁን ደግሞ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ የከተማ ህዝብን ከማገልገል ወደ አገርን ማገልገል መምጣታቸው ትልቅ ሃላፊነትና ትልቅ እድልም እንደሆነ ይናገራሉ።

"እድሉንም በአግባቡ መጠቀም እንዳለብኝ አምናለውም" ይላሉ።

እሳቸው እንደሚሉት አጠቃላይ የሴቶች ሹመቱ በህግ አውጭው በኩል ነገሮች እየተሻሻሉ ቢመጡም በአስፈፃሚው በኩል ግን ከፍተኛ ጉድለት እንዳለ ሲነሳ መቆየቱንና ይህ አዲስ ሹመት ሴቶችን በተለይም በከፍተኛ ደረጃዎች ላይ ማሳተፍን በሚመለከት ያለውን የአፈፃፀም ክፍተት ከመሰረቱ የቀየረና ትልቅ ትርጉም ያለው እርምጃ ነው።

የአዲሱን ሹመት ሃምሳ በመቶ ሴቶች ማግኘታቸውን ብዙዎች በተለያየ መንገድ ተመልክተውታል። የሴታዊት መስራች ዶ/ር ስህን ተፈራ "ሃምሳ በመቶ ሹመት ከጠበቅነውና ማንም መጠየቅ ከሚችለው በላይ ነው" ይላሉ።

በተለይም ትልልቅ የሆኑና ከዚህ ቀደም በወንዶች ይያዙ የነበሩ የሚኒስትር ሃላፊነቶች ለሴቶች መሰጠቱ አስደሳች እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ እርምጃ በደንብ ታስቦቦት የተወሰደ እንደሆነም ያምናሉ ዶ/ር ስህን።

ነገር ግን የሴቶችና የህፃናት ሚኒስቴር የተለያዩ እንዲሆኑ ይፈልጉ እንደነበርና ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሲያብራሩ "የህፃናትና የሴቶች ጥያቄ በጣም ይለያያል ስለዚህ አንድ ላይ እንዲሆኑ ማድረግ ሁሉንም እንደ ተጎጂና ተረጂ የማየት ነገር ነው" የሚል ነው።

በሴቶቹ ሹመት ደስተኛ ቢሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ሴት ተሿሚዎች የተናገሩት ቅር መሰኘታቸውን ግን ይናገራሉ።

"እንደ ዜጋ ሚሰርቁም ማይሰርቁም ስላሉ ዋናው ነገር መሆን ያለበት ሴቶች ይሰርቃሉ፤ አይሰርቁም ሳይሆን ሃምሳ በመቶ ውክልና ስላለን ነው ሹመቱን ያገኙት መሆን ያለበት" ይላሉ።