ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሜክሲኮ ሲቲ የሴቶችን ገላ እየቆራረጡ ሲሸጡ የነበሩ ባልና ሚስት በቁጥጥር ሥር ዋሉ
ባልና ሚስት በቤታቸው የሰው "ስፔርፓርት" ነበራቸው ነው ያለው ፖሊስ። ከሜክሲኮ ወጣ ብላ በምትገኘው ኤካቴፔክ በምትባል ትንሽ መንደር የሚኖሩት ባልና ሚስት የሰው ልጅን አካል እየከታተፉ ለማን ይሸጡ እንደነበር ገና አልተደረሰበትም።
ኾኖም ባልየው ለፍርድ ቤት እንዳመነው ባለፉት ጊዜያት ብቻ 20 ሴቶችን ገድሏል። ሰውነታቸውንም ለገበያ አቅርቧል።
ፖሊስ ባልና ሚስቱ ከሚኖሩበት አፓርትመንት በቅርብ ርቀት በሚገኝ ቤት ያስቀመጧቸውን ገና ያልተሸጡ፣ ነገር ግን የሟቾቹ አካላት እንደሆኑ የተገመቱ የሰውነት ክፍሎችን በብዛት አግኝቷል።
ባልና ሚስቱ እያደኑ ይገድሉ የነበረው ሴቶችን ብቻ እንደነበረም ተመልክቷል።
ይህ ሴቶችን ብቻ የመግደል ድርጊት ሜክሲኮ ገጠራማ ቦታዎች ላይ የተለመደ እንደሆነ ዘገባዎች ያስረዳሉ።
ጎረቤቶቻቸው እንደመሰከሩት ባልና ሚስትን ሁልጊዜም የሚያይዋቸው የሕጻን ማዘያ ጋሪን እየገፉ ነው። ይህም ምናልባት የሟቾችን ገላ የሚሸጡበት ዘዴ እንደሆነ ፖሊስ ጥርጣሬውን ገልጿል።
ጁዋን ካርሎስ በሚል ስም የተጠቀሰው ተጠርጣሪ ሴቶቹን ከመግደሉ በፊት ጾታዊ ጥቃት እንደሚፈጽምባቸው አምኗል። ከዚያ በኋላ ጌጣጌጦቻቸውንና የሰውነታቸውን ክፍል በውል ላልተለዩ ደንበኞች ሲሸጥ እንደነበር ለፖሊስ ቃል ሰጥቷል።
ባልና ሚስቱ በሚኖሩበት አካባቢ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቢያንስ ሦስት አግብተው የፈቱ ሴቶች ከነልጆቻቸው መሰወራቸው ሪፖርት ተደርጎ ነበር። ምናልባትም እነዚህ ሴቶች በነዚህ ባልና ሚስት ተቀጥፈው እንደሆነ ጥርጣሬ አለ። ሕጻናቱን ግን ሳይገድሉ በሽያጭ እንደሚተላለፉ ተጠርጣሪዎቹ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ሜክሲኮ ስቴት ወትሮም ሴቶች ድንገት የሚሰወሩባት ከተማ ናት። በተለይም የመንግሥት ወታደሮች ለመሄድ በሚሰጉባቸውና ወንጀለኞች በሚበዙባቸው ሰፈሮች ሴቶች እንደወጡ ይቀራሉ።
ከጥር እስከ ሚያዚያ ብቻ 395 ሰዎች የት እንደገቡ አልታወቀም። ከነዚህ ውስጥ 207ቱ ሴቶች ናቸው።