የኮፊ አናን ዋና ረዳት ኢትዮጵያዊት እንደነበሩ ያውቁ ኖሯል?

የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን በ80 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት መለየታቸው ከተሰማ ጀምሮ በርካቶች ሃዘናቸውን ሲገልጹ ሰንብተዋል።

በሰብዓዊ ዕርዳታ ሥራቸው የኖቤል ተሸላሚ የነበሩት ኮፊ አናን፤ እአአ 1938 ጎልድ ኮስት ተብላ ትጠራ በነበረችው ጋና ነበር ከመንትያ እህታቸው ጋር የተወለዱት።

ኮፊ አታ አናን ሙሉ ስማቸው ሲሆን አካን በሚባል ቋንቋ የመጀመሪያ ስማቸው ''በዕለተ አርብ የተወለደ'' ማለት ሲሆን አታ ማለት ደግሞ ''መንትያ'' ማለት ነው።

በተባበሩት መንግስታት ሳሉ ለ20 ዓመታት ረዳታቸው ሆነው የሠሩት ኢትዮጵያዊት ወይዘሮ ነበሩ።

ለበርካታ ዓመታት የኮፊ አናን የቅርብ ረዳት በመሆን የሰሩት ወይዘሮ ዋጋየ አሰበ ምንም እንኳ ዛሬ በህይወት ባይኖሩም ሴት ልጃቸው ማርታ ተስፋዬ ስለ ኮፊ አናን የምታስታውሰውን ለቢቢሲ ተናግራለች።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ከመሆናቸው በፊትና ከሆኑም በኋላ ለ22 አመታት አብረው እንደሰሩ ማርታ ትናገራለች።

ማርታ ተስፋዬ ተወልዳ ያደገችው በአሜሪካን ሃገር ዋሽንግተን ዲሲ ነው።

''ወላጅ እናቴ ከኮፊ አናን ጋር ለ22 ዓመታት የቅርብ ረዳት ሆና አብራ ሰርታለች። በርካታ ሃገራትም አብረው ተጉዘዋል'' የምትለው ማርታ፤ ብዙ ጊዜ ኮፊ አናንን በአካል ማግኘቷን ትናገራለች።

ኮፊ አናንን "በጣም ደግ ሰው ነበሩ'' ስትል ትገልጻቸዋለች።

ኮፊ አናን እሷ ወደምትኖርበት ከተማ በመጡ ቁጥር ስልክ ይደውሉላትና ያገኟትም እንደነበር ማርታ ትናገራለች።

''ቀስ ብሎ ነው የሚያወራው። ሲናገር ግርማ ሞገስ ነበረው። ልጅ እያለሁ ''አንክል ኮፊ'' (አጎቴ ኮፊ) ብለሽ ጥሪኝ ይለኝ ነበር'' ትላለች ማርታ።

ወላጅ እናቷ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ 4 ዓመት እንደሆናቸው የምትናገረው ማርታ፤ የኮፊ አናን ሞት ስትሰማ እጅጉን ማዘኗን ትገልጻለች።

''በህይወት ሳለ በርካታ መልካም ነገሮችን ሰርቷል። ብዙ ሰው እንዲህ አይነት ተግባር በህይወቱ መፈጸም ይከብደዋል። እሱ ግን ያንን ፈፅሟል።'' ትላለች።

''ኒውዮርክ ወደሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ዋና መስሪያ ቤት በሄድኩ ቁጥር 38ኛ ፎቅ ላይ ሆኖ፤ ሙሉ ሱፍ ለብሶ እና ጥቁር ገብስማ ጸጉሩ አይረሳኝም'' ትላለች።