በጂግጂጋ የህክምና ቁሳቁሶች እጥረት አሳሳቢ ሆኗል

ጅግጅጋ

የፎቶው ባለመብት, BBC Somali

ሰሞኑን በሶማሌ ክልል ጂግጂጋ የተከሰተውን ብጥብጥ ተከትሎ የህክምና ቁሳቁሶች እጥረት እንዳለ በክልሉ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ በበጎ ፈቃደኛነት የሚያገለግሉ ጠቅላላ ሐኪም ዶ/ር እዮብ መኮንን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በወቅቱ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት በጅግጅጋ ከተማ ከጥቂት ቀናት በፊት አንስቶ በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት ከቤታቸው ተፈናቅለው በቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስትያን ውስጥ ለተጠለሉ እና አካላዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ነው።

ትናንትና ከእኩለ ቀን ትንሽ ቀደም ብሎ በቤተ ክርስትያኒቱ ቅፅር ግቢ ውስጥ ድንኳን ተክለው የህክምና አገልግሎቱን መስጠት መጀመራቸውን የሚናገሩት ዶክተር እዮብ ቢቢሲ እስካናገራቸው የዛሬ ረፋድ ድረስ ባለው ጊዜ ከመቶ በላይ ለሚሆኑ ጉዳተኞች እርዳታ መስጠታቸውን ይናገራሉ።

ይሁንና ከግጭቱ በፊት አንስቶ ረዘም ላለ በሽታ ተከታታይ ህክምና በመውሰድ ላይ የሚገኙ ተፈናቃዮች ችግር ላይ መውደቃቸውን ያሰምሩበታል።

እነዚህ በሽተኞች "በዚህ በአደጋው ምክንያት መድኃኒታቸውንም አጥተዋል፤ ከቤታቸው ሲወጡ ሁሉንም ነገር ነው ያጡት" ይላሉ። "እዚህ በቂ የመድኃኒት አቅርቦት የለም። የተቻለው እየተደረገ ነው፤ ግለሰቦችም እርዳታ እያደረጉ ነው። ግን በቂ አቅርቦት የለም። እዚህ የስኳር፥ የደም ግፊት በሽተኞች አሉ።"ብለዋል

የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ማኅበር በቤተ ክርስትያኑ ያሰማራው የበጎ ፈቃደኞች ቡድን አምስት ሐኪሞች፣ አምስት ነርሶች እና የመድኃኒት ባለሞያ እንዳለው ዶክተር እዮብ ጨምረው ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ከግጭቱ ጋር በተገናኘ በከተማዋ የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥር ከሃያ ሺህ እንደሚበልጥ መረጃ እንዳላቸው የሚናገሩት ዶክተር እዮብ፥ ገረባሳ በተሰኘ የወታደሮች ካምፕ ውስጥ የተጠለሉ ሁለት ሺህ አካባቢ የሚሆኑ ተፈናቃዮችን በትናንትናው ዕለት መጎብኘታቸውን ይናገራሉ።

በካምፑ ውስጥ ያሉት ተፈናቃዮች ሜዳ ላይ ፈስሰው እንደሚገኙ እና ከወታደሮች ጋር ከመጋራታቸው በስተቀር ሌላ የምግብ ምንጭ እንደሌላቸው ማስተዋላቸውንም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ መምህር በርካታ ሰዎች ከተማዋን ለቅቀው ለመውጣት መኪኖችን ሲማፀኑ መመልከታቸውን እንዲሁም በጭነት መኪና ከመጠን በላይ ታጭቀው ወደሃረር በማቅናት ላይ ያሉ በርካቶች መኖራቸውን በወሬ መስማታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

መምህሩ የኢንተርኔት አግልግሎት መቋረጥ ችግሩን እያባባሰ ነው ባይ ናቸው።

በአንድ በኩል ከየት እንደሚመጡ የማይታወቁ መረጃዎች ለሰዎች ዘንድ በስልክ መድረሳቸው ያለውን ስጋት ያናረው ሲሆን፥ ትክክለኛ እና ተጨባጭ መረጃ ከማግኘት እንደታቀቡ ይገልፃሉ።

"ህዝቡ ምንም መረጋጋት አልቻለም። ለምሳሌ ትናንትና መነሻ የማይታወቅ መረጃ ተነዝቶ፤ ትጥቅ የማስፈታት ሂደት ስለሚኖር የተኩስ ልውውጥ መፈጠሩ አይቀርም በሚል ሰዎች ሁሉ እየተደዋወሉ በስጋት ሲናጡ ነው ያመሹት"ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ያለውን ችግር ጥልቀት በአገሪቱ ዙርያ ለማሳወቅ እና አፋጣኝ እርዳታ እንዲሁም መፍትሔ እንዳይመጣ ደንቃራ ፈጥሯል ይላሉ።

"የኢተርኔቱ መቋረጥ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥሯል። ቢያንስ ያለውን ነገር፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አልፎም ለዓለም ሕዝብ ማሳየት ይቻል ነበር።" ይላሉ።