ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኤርትራ ልዑካን ቡድን አባላት አዲስ አበባ ደርሰዋል
በኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልሕና የፕሬዝዳንቱ አማካሪ በሆኑት የማነ ገብረ አብ የሚመራው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ገብተዋል።
ለልኡካን ቡድኑ በቦሌ አየር ማረፊያ በመገኘት አቀባበል ያደረጉላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ፣ የኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑት አቶ አህመድ ሽዴና አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) ናቸው።
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ባለፈው ሳምንት በኤርትራ ቴሌቪዥን የሰማዕታት ቀንን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር ስለአገራቱ የወደፊት ጉዞ የሚመክር አንድ የልዑካን ቡድን ወደ አዲስ አበባ እንደሚልኩ መግለፃቸው ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ መለስ አለም አርብ ዕለት በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የሚኖር ሰላም ከሁለቱ አገራት ባለፈ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት በጣም ጠቃሚ እንደሆነ "ፋይዳው ከክልሉ በላይ ነው" በማለት ነበር የተናገሩት።
ጨምረውም በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ለኤርትራ ልዑካን አቀባበል ለማድረግ ዝግጅት እንደሚኖር ተናግረው ነበር።
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የሰማዕታት ቀንን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር ላይ እንደገለፁት የልዑካን ቡድኖቹ ወደ አዲስ አበባ የሚያቀኑት ጉዳዩን በቀጥታና በጥልቀት ለማወቅና ቀጣይ የስራ እቅድ ለማውጣት እንደሆነም ጨምረው ተናግረዋል።
የኤርትራን የልዑካን ቡድን ለመቀበል በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ የነበረው ድባብ ይህን ይመስላል።