የካናዳ ፓርላማ ዕፀ-ፋርስን ለመዝናኛነት ህጋዊ አደረገ

የካናዳ ሰንደቅ ዓላማ የዕፀ-ፋርሰ ቅጠል ጋር

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty

የካናዳ ምክር ቤት ዕፀ-ፋርስን ለመዝናኛነት ህጋዊ አድርጓል።

ምክር ቤቱ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው ማክሰኞ ሲሆን ህጉ ዕፀ-ፋርስ እንዴት እንደሚበቅል፣ እንደሚሰራጭና እንደሚሸጥም ይወስናል።

ይህ ህግም ካናዳውያን ከመጪው መስከረም ጀምሮ ዕፀ-ፋርስን በህጋዊ መንገድ መገበያት ያስችላቸዋል።

ዕፀ-ፋርስን ለመዝናኛነት ህጋዊ ስታደርግ ካናዳ ሁለተኛ አገር ናት።

ኡራጓይ በአውሮፓውያኑ 2013 ተክሉን ለመዝናኛነት ህጋዊ ያደረገች ሲሆን ፤ በተቃራኒው የአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ተቃውመውታል።

በካናዳ ዕፀ-ፋርስን መጠቀም ወንጀል የሆነው በአውሮፓውያኑ 1923 ሲሆን ለህክምና አገልግሎት ፈቃድ ካገኘ 17 ዓመታትን አስቆጥሯል።

አዋጁ በዚህ ሳምንት ህግ ሆኖ ከፀደቀ በኋላ መንግሥት ህጉ ተግባራዊ የሚሆንበትን ኦፊሴላዊ ቀንም ይወስናል።

የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ በትዊተር ገፃቸው እንዳሰፈሩት "ለልጆቻቸችን ዕፀ-ፋርስን ማግኘት ቀላል ነበር፤ ወንጀለኞችም ትርፍ በማጋበስ ላይ ናቸው" ብለዋል።

በተቃራኒው አንዳንድ ቡድኖች ይህንን አዋጅ የተቃወሙ ሲሆን በተለይም ተቃዋሚ ወግ አጥባቂ ቡድን በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ድምፅ አሰምተዋል።

መንግሥት ግዛቶቹን እንዲሁም ለአስተዳደሮቹ ከ8-12 ሳምንታት በመስጠት ለዕፀ-ፋርስ የገበያ ቦታ እንዲያመቻቹ ጊዜ እንደሚሰጥም አሳውቀዋል።

ይህ ጊዜም ለኩባንያዎች ብቻ ሳይሆን ለፖሊስ ኃይልም አዲሱን ህግ ተግባራዊ እንዲያደርጉት ጊዜ እንደሚሰጥም ተገልጿል።

ከሶስት ዓመታት በፊት የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ካናዳውያን ለዕፀ-ፋርስ ስድስት ቢሊዮን ዶላር እንዳወጡ ተገልጿል።