ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሠዐሊ እያዩ ገነት "ሀገሬ ራሱ በድንቅ ተቃርኖ ውስጥ ተዛንቃ ስላለች ሥራዎቼም እንደዛ ናቸው"
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህሩ እያዩ ገነት ሥዕልን እንጀራዬ ብሎ ከመያዙ በፊት የምጣኔ ሐብት ባለሙያ ነበር። ሥዕልን መሳል የጀመረው በተፈጥሯዊ ግፊት እንደሆነ የሚናገረው እያዩ በልጅነት እድሜው ''ነገሮችን ከጽሁፍ ይልቅ በምስል ስመለከት በቀላሉ እረዳ ነበር'' ይላል።
የምጣኔ ሐብት ባለሙያ ሆኖ ተቀጥሮ ሥራ ቢጀምርም የውስጥ ስሜቱ ግን የሚነግረው ሠዐሊ መሆኑን ስለነበር ወደ አዲኢስ አበባ በመምጣት ዩኒቨርስቲ ገብቶ ስዕልን አጠና።
ከዱርቤቴ አቅራቢያ በምትገኘው ጉራች ጊዮርጊስ የተወለደው እያዩ፤ አሁን ለሚገኝበት ደረጃ የአባቱ አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል እንዳልነበር ይገልፃል። አባቱ የልጅነት ፍላጎቱን ነገሮችን በምስል የመግለፅ ንሸጣውን እያዩ የማበረታቻ ሽልማት እየሰጡ ተሰጥኦውን መኮትኮታቸውን ያስታውሳል።
እያዩ ነፃ እና ፍቅር በተሞላ ቤተሰብ እና ዘመድ መሀል ነው ያደግኩት በማለት ገጠር ማደጉ ለጥበብ ሕይወቱ ትልቁን አስተዋፅዖ እንዳደረገ ይናገራል።
''ማህበረሰቡ አንድን አርቲስት ጥሩ አርቲስት ነው ብሎ የሚያስበው የአንድን ነገር ተፈጥሯዊ ምስል ሳይቀይር ወይም ሳያዛባ ሲያስመስል ነው'' የሚለው እያዩ በልጅነት እድሜው ይህ አውንታዊ የአሳሳል ዘውግ ተቀባይነት ስለነበረው እሱም የታዋቂ ግለሰቦችን ፎቶግራፎች አስመስሎ በመስራት ከቤተሰቡ እና ከአካባቢው ማህበረሰብ ሁሉ አድናቆትን ያገኘ እንደነበር ያስታውሳል።
ሁነኛ ሃሳብ ገላጩ ጽሑፍ ወይስ ሥዕል?
ለእያዩ ምስል ከየትኛውም የሃሳብ ማራመጃ መንገዶች መካከል ጉልበታሙ ነው። የምስልን ጉልበት ከተረዳን ሥዕል ከጽሑፍ በተሻለ ሁኔታ ሃሳባችንን ሊገልጽልን ይችላል ባይ ነው።
እንደ እያዩ አተያይ በአንድ ሰው አዕምሮ ውስጥ አንድ ሃሳብ ሲፈልቅ፣ ሃሳቡ ቀድሞ በምስል መልክ በአዕምሮው ውስጥ ይቀረጻል።
''አንድ ደራሲ ድርሰቱን ሲጽፍ በድርሰቱ ውስጥ ያሉትን ገጸ-ባህሪያትን ቀድሞ በአዕምሮው ውስጥ ይስላቸዋል፤ ከዚያም በአዕምሮ ውስጥ የሳላቸውን በጽሑፍ ከወረቀት ጋር ያገናኛቸዋል'' ይላል።
እያዩ ብሩሽን ከሸራ ጋር ሲያገናኝ መንፈሳዊ ሙዚቃዎችን እያደመጠ መሳል ይወዳል። ይህ ግን የውጭውን አለም ረብሻ ለማስቀረት እንጂ ነገሮች ፀጥ ካሉ በፀጥታው ውስጥ ተመስጥኦውን በመፈለግ መሳል ይመርጣል።
ሥራዎቹን ያቀረበባቸው መድረኮች
በሀገርም ውስጥ ሆነ ከሀገር ውጭ በርካታ አውደ ርዕዮችን ላይ የተሳተፈው እያዩ በሀገር ውስጥ በብሔራዊ ሙዚያም እና በርካታ መድረኮች ላይ በግልና በቡድን ሥራዎቹን አቅርቧል።
ከኢትዮጵያም ውጪ በአሜሪካንና በኢኳዶር የሥዕል ሥራዎቹን ማሳየት ብቻ ሳይሆን አብሮ ለውይይት የሚሆኑ ፅሁፎችን ያቀረበባቸው መድረኮች እንዳሉም ያስታውሳል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊትም በጉራማይሌ የአርት ማዕከል ውስጥ ''ነቁጥ'' በሚል ርዕስ ሥራዎቹን ለህዝብ አሳይቷል።
በእያዩ የሥዕል ሥራዎች ላይ ቆዳ ትልቅ ቦታ ይዞ ይታያል። በርካታ ሥዕሎቹም በቆዳ ላይ ነው የተሳሉት።
''እኔ ያደኩበት ማህበረሰብ የቆዳን ሥነ-ውበት ጠንቅቀው ያውቁታል። አንድን በሬ አርደው ስጋውን ከበሉ በኋላም ቢሆን ቆዳውን አለስልሰው ይሰቅሉታል። በዚህም ፍቅራቸውን እና ተፈጥሯዊ ግንኙነታቸውን ይገልጹበታል። እኔም ይህን ቁርኝነት በሥራዎቼ ላይ ግብአት አድርጌ እጠቀምበታለሁ" ይላል።
የዓለም ህዝብ የራሱ የሆነ ባህል እና የሥነ-ጥብብ መገለጫ አለው የሚለው እያዩ የስዕል ሥራዎቹ በምዕራብውያን ተጽእኖ ስር እንዳይወድቁ ይጠነቀቃል።
ለእያዩ ማህበረሰቡ በተለምዶ የሚሰራቸው የጥበብ ሥራዎች ተራ የዕደ-ጥበብ ውጤቶች ብቻ አይደሉም ሲል ይሞግታል፤ ''እነዚህም ሥነ-ጥበብ ነው'' የሚባሉት ሲል ተራው ማህበረሰብ የሚሰራው እና የጥበብ እጁን ያሳረፈበት ምርጥ የጥበብ ሥራ እንደሆነ ያብራራል።
አክሎም እኔም ሥራዎቼን ባለው እሴት ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊ ወይም ማህበራዊ ፍንጭ ሰጥቼና ጨምሬበት ነው የምሰራው ሲል ስለሥራዎቹ ያስረዳል።
ኢትዮጵያውያን ወካይ አሳሳል ስልት እንከተላለን የሚለው እያዩ በሀገሪቱ ያሉ ጎብኚዎች የሚያዘወትሯቸው ስፍራዎች ላይ የሚገኙ የስዕል ውጤቶች ቢታዩ ይህ ነገር እንደሚጎላ ይናገራል።
''ታዲያ እኔም ኢትዮጵየያዊ ከሆንኩ እና ከዚህ ሰፊ ባህር ከተጨለፍኩ እንደምን ውክልናን ከስዕሌ ማስቀረት ይቻለኛል?'' በማለት በሬን እና ቀንዱን በስዕሎቹ ውስጥ ለውክልና ተጠቀሞበታል። ከበሬም ይላል እያዩ ግንባሩ፣ ፊት ለፊት የሚታየው አካሉ ላይ ያተኩራል።
ይህ ሁለት ሀሳብ ይወክልልኛል የሚለው ሠዐሊ እያዩ ቀዳሚ ሀሳቡ የአሸናፊነት እና የተማፅኖ ድምፅን እንዲወክልልኝ አድርጌ ነው የምጠቀምበት ይላል።
የአሳሳል ስልት
እያዩ በአሳሳል ዘዬው ቅፅበቶችን በሸራ ላይ ማስቀረት እንደሚፈልግ ይናገራል። "በስዕሎቼ በቅፅበቶች ውስጥ የተሰማኝን ስሜት ለመግለፅ የትኛው መንገድ ይሻለኛል የሚለውን እመርጣለሁ።"
በዓውደ ዓመት ወቅት እንደ ኪነ-ጥበብ ባለሙያ ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያዊ እና እንደ ሐይማኖተኛ ሰው እውናዊው አሳሳል የሚገልፅልኝ ሆኖ ሳገኘው እርሱን እጠቀማለሁ ይላል።
''በእርግጥ አንዳንድ ሀሳቦች ሰወር ብለው በተመልካች ዘንድ ጥያቄና የአእምሮ ሙግት ቢፈጥሩ ብዬ ሳስብ ወደ አብስትራክት ቀረብ ያሉ ስዕሎችን መሳል እመርጣለሁ'' የሚለው እያዩ ''ለእኔ የሚመቸኝ ግን ዓለም ራሱ በአብስትራክት እና በእውነታ መካከል ስለሆነች ሁለቱን አዛንቆ መሳል ነው።''
''የምናየውን እውነታ ሁሉ ጠጋ ብለን ስናየው አለ ያልነው ነገር በውስጡ የለም'' የሚለው እያዩ በከፊል እውናዊ የሆነውን አሳሳል መጠቀም ይመርጣል። በአሳሳል ረገድም ብዙ ነፃነት ይሰጠኛል ብሎ ያምናል።
"ሀገሬ ራሱ በተቃርኖ ውስጥ ተዛንቃ ስላለች ሥራዎቼም እንደዛ ናቸው እላለሁ።"
በሥራዎቼ ባህላዊ የሚባሉ ነገሮችን ወስጄ ከጀርባው ደግሞ በጣም ዘመናዊ ሃሳብን በማምጣት በሸራዬ ላይ ተዋደውና ተጋምደው እንዲቀመጡ አደርጋለሁ የሚለው እያዩ ይህ የአሳሳለ ዘይቤው በሥራዎቹ ውስጥ ሁሉ ዱካው እንደሚገኝ ይጠቅሳል።
ጥበብን መረዳት
ሥዕል ለአይን ብቻ ሊሰራ ይችላል የሚለው እያዩ ጠያቂ፣ ስልተምት ያለው ለተመልካቹ የማሰብና የመመርመር እድል የሚሰጥ መሆን እንዳለበት ያምናል።
ሰዎች እንደኖሩበት ባህልና ማህበረሰብ አንድን ሥራ ሊረዱት ይገባልም ባይ ነው።
አንድ የኪነ-ጥበብ ባለሙያ ሥራው ከእጁ ከወጣ በኋላ የእርሱ ሳይሆን የተመልካች የተርጓሚው ነው ሲል ሃሳቡንም ያጠናክራል። የአንድ ሥራ ታዳሚ ልጓም ሊበጅለት አይገባም ሲልም አፅንኦት ይሰጣል።