ተማሪዎች አስገድዶ ስለመድፈር በመቀለዳቸው ታገዱ

የፎቶው ባለመብት, Alamy
አስራ አንድ የዋርዊክ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ሴቶችን አስገድዶ ስለመድፈር በፌስቡክ ላይ በመቀለዳቸው ከተቋሙ ታገዱ። ተማሪዎቹ እርምጃ የተወሰደባቸው በፌስቡክ የቡድን መነጋገሪያ ገፅ የተጻጻፉት መልእክት ይፋ ከወጣ በኋላ ነው።
ተማሪዎቹ የተለዋወጧቸው የጽሁፍ መልዕክቶች ፎቶ ተነስተው ይፋ የተደረጉ ሲሆን፤ ተቋሙ ጉዳዩን እየመረመረ መሆኑን ገልጾ ተማሪዎቹ "የሥነ-ምግባር ማረሚያ ቅጣት ይጠብቃቸዋል" ተብሏል።
የተቋሙ ቃል አቀባይ "እያደረግን ያለው ምረመራ ሳይጠናቀቅ ስለጉዳዩ ተጨማሪ አስተያየት መስጠት እንችልም" ብለዋል።
ተማሪዎቹ የተለዋወጧቸው መልዕክቶች ይፋ የሆኑት 'ዘ ቦር' እና 'ዘ ታብ' በተሰኙ የተቋሙ የድረ-ገጽ ጋዜጦች ላይ ነው።
ከተማሪዎቹ አንዱ 100 ሴቶችን አስገድዶ ስለመድፈር "አንዳንዴ ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ 100 ሴቶችን መድፈር ያዝናናል" በማለት ጽፏል። ሌላው ተማሪ "ሁሉንም ሴቶች ደፍሮ ልክ ማስገባት ነው" ብሏል።
ተማሪዎቹ በተለዋወጧቸው መልዕክቶች አንዱ "ሰው ሁሉ የሚያይበት አውላላ መንገድ ላይ ድፈራት" ሲል ሌላው "ምንም ችግር የለውም" ብሎ መልሶለታል።
ተማሪዎቹ ዘረኛ መልዕክቶችም ተለዋውጠዋል። "ሒትለርን እንወደዋለን፤ አይሁዳዊያንን እንጠላለን" የሚለው ይጠቀሳል።
ከተቋሙ የድረ-ገጽ ጋዜጦች አንዱ የሆነው 'ዘ ታብ' አርታኢ ሮሂኒ ጃስዌል "ጽሁፎቹን ሳነብ መላ ሰውነቴ ተረብሿል" በማለት ድንጋጤዋን ገልጻለች።
የመጀመሪያ ዓመት የታሪክና ፖለቲካ ተማሪ የሆነችው የ18 ዓመቷ ሮሂኒ ተቋሙ በአፋጣኝ እርምጃ አለመውሰዱን ተናግራለች።
የተቋሙ የተማሪዎች ቃል አቀባይ ተግባሩን አውግዛ "ጉዳዩ በቶሎ እልባት እንደሚሰጠው ተስፋ እናደርጋለን። የተማሪዎች ሕብረት የጽሁፍ መልዕክቶቹ ቃላዊ ጥቃት ያደረሰባቸው ተማሪዎችን እስከመጨረሻው ይደግፋል" ብላለች።
'ዘ ቦር' የድረ-ገፅ ጋዜጣ ትዊተር ላይ ያሰፈረው መልዕክት ተቋሙ ስለወሲባዊ ጥቃት ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንዲያዘጋጅ ያሳስባል።
የእንግሊዙ ዌስት ሚድላንድ ፖሊስም "በጉዳዩ እጃችንን ከማስገባታችን በፊት እያጣራን ነው" ብሏል።
በታይምስ የዘንድሮው የዓለም ከፍተኛ ተቋሞች ዝርዝር የዋርዊክ ዩንቨርስቲ አስራ አንደኛ ደረጃ ተሰጥቶታል።












