ካለሁበት 28፡ "ያደግኩበት አካባቢና የሰፈሬ ልጆች በጣም ይናፍቁኛል"

የፎቶው ባለመብት, Musie Risom
ስሜ ሙሴ ርዕሶም ይባላል። ከኤርትራ የወጣሁት ሃገሬን ጠልቼ ሳይሆን እንደ አብዛኛው ኤርትራዊ ማለቂያ የሌለውን የውትድርና ልምምድ በመቃወም ነው።
በረሃውንና ባህሩን አቋርጬ፣ ከብዙ ፍዳ በኋላ 2002 ላይ እንግሊዝ መግባት ቻልኩ። እንግሊዝ ውስጥ የመኖሪያ ፈቃድ ማግኘት እጅግ የከበደ እና ብዙ ውጣ ውረድ ያለው ቢሆንም የምፈልገውን ከማድረግ አልገታኝም።
አሁን ላለሁበት ስኬት ለመድረስ ብዙ ፈተናዎችን ማለፍ ነበረኝ። ያሳልፈኳቸው ተዘርዝረው የማይልቁ ውጣ ውረዶች ነገሮችን በትዕግስት ማድረግ እንዳለብኝ እንድማር አግዘውኛል።
እንግሊዝ ከገባሁ በኋላ አስፈላጊውን መመዘኛ በማሟላት የኤሌክትሪክ ምህንድስና ትምህርቴን ተከታትዬ አጠናቀቅኩኝ። ከዚያም ከፍቅር ጓደኛዬ ጋር ትዳር ከመሠረትን በኋላ ወደ ኖርዌይ ገባሁ፤ እርግጥ ነው የኖርዌይን ቋንቋ ለመማር ትንሽ ጊዜ ወሰዶብን ነበር።
ኖርዌይ መኖር ከጀመርን ከጥቂት ጊዜያት በኋላ በአንድ የነዳጅ ማጣሪያ ኩባንያ በትምህርቴ የቴክኒክ ባለሙያ ሆኜ መሥራት ጀመርኩ።
ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ እሠራበት ከነበረው መሥሪያ ቤት ለቅቄ ኦስሎ ከተማ ውስጥ 'ዱባይ ጠቅላላ አገልግሎት' የሚባል ሱቅ ከፍቼ የንግድ ሥራን ተቀላቀልኩ።

የፎቶው ባለመብት, Musie Risom
ኖርዌይ ውስጥ የሌላ ሃገር ዜጋ ሆኖ እንደዚህ ዓይነት ሥራ መሥራት በጣም ከባድ ቢሆንም ህልሜ ትልቅ በመሆኑ ማድረግ ችያለሁ።
የምኖርበት አካባቢ ለዓይን በሚማርኩ ተራራዎች የተከበበ በመሆኑ ሁልጊዜ ከቤተሰቦቼ ጋር በመስኮት አሻግሬ የማየው አስደናቂ ተፈጥሮን ቢሆንም በኦስሎ ሱቄ ውስጥ ሆኜ አሻግሬ የማየው ግን መጪውን ዕድሌንና እድገቴን ነው።
ተራራዎች ኤርትራና ኖርዌይን የሚያመሳስሏቸው ቢሆንም አጥንት በስቶ የሚገባው የኖርዌይ ብርድና በረዶ ከሃገሬ ሙቀት ጋር የሰማይና ምድር ያህል ልዩነት እንዳላቸው እንዲሰማኝ ያደርገኛል።
በማሕበራዊ ኑሮም ኤርትራ እና ኖርዌይ ሰፊ ልዩነት አላቸው። ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ የኖርዌይ ሰዎች የግላዊ የሕይወት አዙሪት ውስጥ ያሉና ብዙም ከሰው ጋር ቁጭ ብሎ የማውራት ባህል የሌላቸው መሆኑ ነው።
ጮክ ብለው እንኳን አይናገሩም። የቅርብ ጎረቤት መተዋወቅ በራሱ ከባድ ነው፤ ሁልጊዜ የቤታቸው በር ዝግ ነው።
በሥራም ሆነ በትምህርት የሚያውቁት ሰው ከእነዚያ ቦታዎች ውጪ እንግዳ ነው፤ አትኩሮ ብቻ ይመለከትዎታል። መጀመሪያ በጣም ይከብደኝና ያናድደኝ ነበር፤ ሳስበውም ያስገርመኝ ነበር፤ አሁን ግን ለምጄዋለሁ።
እዚህ የምንኖር ኤርትራውያን እርስ በራሳችን መልካም የሚባል ግንኙነት አለን፤ በደስታም ሆነ በሐዘን እንረዳዳለን። በቤታችን ውስጥ አንዳንድ ጊዜ እንጀራና ሌሎች ሃገራዊ ምግቦችን እናዘጋጃለን። ቢሆንም ግን እንደ ሃገር ቤት በፍፁም አይሆንም። ብዙ ጊዜ ግን ጨው ጨው የሚልና ደርቆ ለብዙ ጊዜ የሚቆይ የኖርዌይ ምግብ ነው የምንመገበው።
ከዓሣ፣ አትክልትና ሥጋ የተሠራ ፓስታ በጣም ነው የምወደው።
ከልጅነቴ ጀምሮ እግር ኳስ መጫወት እወዳለሁ። " ምድላው መግቢ" ለሚባል እግር ኳስ ቡድን እጫወትም ነበር። ይሄና ሌሎች ትዝታዎች አንድ ላይ ሆነው ያደግኩበትን አካባቢና የሰፈሬን ልጆች በጣም እንድናፍቅ ያደርጉኛል።
ወደ ሃገር ቤት የመሄድ ዕድል ቢያጋጥመኝ ተወልጄ ባደግኩባት ውቢቷ አስመራ ከተማ ከቤተሰቦቼ ጋር ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ እፈልጋለው።

ለኤደን ሃብተሚካኤል እንደነገራት
የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍል ለማግኘት ፦














