ካለሁበት 29 ፡ እዚህ ሰው በሰውነቱ ብቻ ትልቅ ክብር አለው፤ ሃሳቡን በመናገርም ሆነ በሌላ ነገር ለመግለጽ ቢሻ ገደብ አይበጅለትም።

ለሚ በትምህርት ቤት

የፎቶው ባለመብት, Lammi T. Nagawoo

የምስሉ መግለጫ, ለሚ በትምህርት ቤት

ለሚ ተክሌ እባላለሁ። አሁን የምኖረው አምየን በምትባል የፈረንሳይ ከተማ ሲሆን የምትገኘው ከፓሪስ 120 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ነው።

ከኢትዮጵያ ስወጣ በኬንያ አድርጌ ነበር። ከዚያም ኬንያ ትምህርቴን አጠናቅቄ ሁለተኛ ዲግሪዬን ጀምሬ አንድ ዓመት እንደጨረስኩኝ ችግር ገጥሞኝ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ግድ ሆኖብኝ ነበር።

ሆኖም ግን ያሰብኳቸውን ነገሮች መሥራት ባለመቻሌ ወደ ናይሮቢ ተመልሰኩኝ። የነበርኩበት ሁኔታ ትምህርቴን የሚያስቀጥል ባለመሆኑ አስቸጋሪና ውስብስብ የስደት ጉዞ ለማድረግ ተገደድኩኝ።

ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ

ከኬንያ ወደ ኡጋንዳ ከዚያም በደቡብና ሰሜን ሱዳን ቆላማው ክፍል አድርጌ ሰሃራ በረሃን አቋርጬ ግብፅ መዲና ካይሮ ገባሁ።

ካይሮ ትንሽ ከቆየሁኝ በኋላ በሜዲቴራንያን ባሕር አድርጌ ወደ ጣልያን ለመግባት ወሰንኩኝ። ጉዞው አስቸጋሪና አስፈሪ ስለሆነ ከባድ ውሳኔ ላይ እንደደረስኩኝ አውቅያለሁ። ሆኖም ግን እራሴን አጠንክሬ ጉዞዬን ማድረግ ነበረበኝ።

ሁለት ሳምንት በባሕር ላይ ስንቆይ አስፈሪነቱ እየተገለጠልኝ መጣ። በቅብብሎሽ የሚደረግ ጉዞ በመሆኑ በመጀመሪያ ትናንሽ መርከቦች ከካይሮ ወሰዱንና ወደ ጥልቅ ባሕር እንደደረስን ወደ ትልቅ መርከብ አስተላለፉን።

ቀሰ በቀስ ወደ ጣሊያን ተጠግተን የውሃ ድንበሯን እንዳቋረጥን በጣሊያን ድንበር ጠባቂ ፖሊሶች ቁጥጥር ሥር ዋልን። ከዚያ ግን ፈረንሳይ ለስደተኞች ጥሩ ሃገር ናት ሲባል እሰማ ስለነበር እንደምንም ብዬ ወደዚያ ለመሄድ ወሰንኩኝ። በመጨረሻም ተሳካልኝና ፈረንሳይ ገባሁ።

ባሕር ላይ ፈተና

ባሕር ላይ በርካታ ችግሮች ያጋጣማሉ። የምግብና ውሃ እጥረት፣ የመርከብ ሞተር መበላሸትና መርከቡ ወዳልተፈለገበት አቅጣጫ በንፋስ መወሰድ የመሳሰሉት ችግሮች ሲያጋጥሙን ነበር።

እኔም የነበርኩበት መርከብ ሞተር መሃል ውቅያኖስ ላይ ብልሽት ደረሰባት። ብዙ ጥረት ተደርጎ ከተሠራች በኋላ ከአንድ ቀን በኋላ መንገዳችንን ቀጠልን። በተመሳሳይ ሁኔታ ደግሞ ጓደኞቼ የነበሩበት መርከብ ሞተሩ ተበላሽቶ መሃል ውቅያኖስ ላይ ቆሞ ደረስንበትና በእኛ መርከብ እየተጎተተ የሄደበትን አጋጣሚ አልረሳውም።

በጣም የሚያሳዝነው ከእኛ አንድ ሳምንት ዘግይቶ ይነሳ የነበረ መርከብ ጓደኞቻችንን እንደያዘ የት እንደገባ ሳይታወቅ እንደጠፋ መቅረቱ ነው። ስንገምት ወይ መርከቡ ሰጥሞ ነው ለበለዚያ ደግሞ ኩላሊት በሚሰርቁት ሰዎች በግዳጅ ተወስዶ ሊሆን ይችላል። በሌላ ባሕር ዳርቻ ደርሶ በቁጥጥር ሥር ወድቆም ሊሆን ይችላል፤ እኛ ግን ምንም ማወቅ አልቻልንም ነበር።

ለሚ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ይማራል

የፎቶው ባለመብት, Lammi T. Nagawoo

ይህን ሳስብ ሁልጊዜ ያበግነኛል። እስከ መቼ ነው ወገኖቼ በባሕር እየተሰደዱ እስከመቼ እንደረገፉ ይቀራሉ ብዬ እራሴን እጠይቃለሁ። በተለይ ይህን እንዳስብ ሁሌም የሚያስገድደኝ እራሴው በዚህ መንገድ ማለፌ ነው።

የዚህ ሃገር ሥልጣኔና እድገት እንዳለ ሆኖ፤ በፈረንሳይና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ትልቁ ልዩነት ሰላም፣ ዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ነው። እዚህ ሰው በሰውነቱ ብቻ ትልቅ ክብር አለው፤ ሃሳቡን በመናገርም ሆነ በሌላ ነገር ለመግለጽ ቢሻ ገደብ አይበጅለትም።

እዚህ ከመጣሁ አንስቶ መመገብ የሚያስደተኝ ፒዛ ነው። የሚጣፍጥ ፒዛ ያዘጋጃሉ።

ፒዛ

የፎቶው ባለመብት, Lammi T. Nagawoo

መቼም ከእራስ ሃገር ሁሉም ነገር ይናፍቃል። ዛፉ፣ ሰዉ፣ ከብቱ፣ ባህሉና ወጉ፣ ማሕበራዊ ኑሮው የእርስ በእርስ መከባበሩ፤ በተለይ ደግሞ አብሮ መብላቱ፣ በዓላቱን አብሮ ማሳለፉ።

ምክንያቱም የእኛ ሃገር ሰው ብቻውን አይበላም፤ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች በጣም ይናፍቁኛል።

የአምየን ከተማ ጥንታዊና ታሪካዊ ከተማ በመሆኗ በብዙዎች ዘንድ ትታወቃለች። በተለይ በትልቁ የጎቲክ ካቶሊክ ካቴድራሏ የበርካቶችን ቀልብ የሚስብ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ለሃገሪቱ በተዋጉ የጥንት አርበኞች የተመሠረተች ከተማ ነችም ይባልላታል።

እዚህ የምትገኘው ትልቋ የካቶሊክ ካቴድራል 3000 ዓመታትን አስቆጥራለች ይባላል። ይህ በጣም ትልቅ ቤተክርስቲያን ታሪካዊ ከመሆኑም ባሻገር በጣም የሚያምርም ስለሆነ በጣም የምንወደው ሥፍራ ነው።

እዚህ ሃገር ከመጣሁ ቀልቤ አርፏል፤ ብዙ ነገሮች ተሳክተውልኛል። ትልቁ ነገር ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ጉዳዬ በመንግሥት ተቀባይነት አግኝቶ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ ማግኘቴ በጣም ካስደሰቱኝ ነገሮች አንዱ ነው።

በአምየን የምትገኘው የካቶሊክ ካቴድራል

የፎቶው ባለመብት, Lammi T. Nagaawoo

የምስሉ መግለጫ, በአምየን የምትገኘው የካቶሊክ ካቴድራል

ብዙ ሰዎች ይህንን ሳያገኙ ከአሥር ዓመታት በላይ የኖሩ አሉ፤ እኔን እግዚአብሔር በጣም እንደረዳኝ ይሰማኛል።

የፈረንሳይ አረንጓዴ መሆን ያደግኩበትን ምዕራብ ወለጋን ያስታውሰኛል። ወደዚህ ሃገር እንደመጣሁ ቋንቋውን አለመቻሌ ትልቅ ችግር ሆኖብኝ ነበር። አሁን ግን የተወሰነውን ለመማር ችያለሁ። በርትቼም መማሬን እቀጥላለሁ።

በአንዴ ወስዶ ሃገሬ ላይ ሚጥለኝ ሁኔታ ቢፈጠር ድንገት እራሴን ሃገሬ ላይ ማግኘት እሻለሁ። እንደው ተወልጄ ያደግኩበትና ቤተሰቦቼን፣ ዘመዶቼና ጓደኞቼ የሚገኙበት ምዕራብ ወለጋ ዱብ ብል ደስ ይለኛል።

Presentational grey line

ለጫሊ ነጋሳ እንደነገረው

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍሎችን ለማግኘት ፦