'ለመጥፋት አደጋ የተጋለጠው' የኢትዮጵያ ህትመት ሚድያ

ነዋሪነቷን ኬንያ መዲና ናይሮቢ ያደረገችው አልባብ ሰይፉ ዘወትር ማለዳ ከመኖሪያ ቤቷ ወደ ሥራ ስታቀና አንድ ነገር ትታዘባለች። የትራፊክ መጨናነቅ የማይለያት ናይሮቢ ነዋሪዎች በህዝብ ትራንስፖርትም ሆነ በግል መኪናዎቻቸው ሆነው ጋዜጣ እያገላብጡ ሲጓዙ።

"ናይሮቢያዊያን ከጋዜጣ በሚያገኙት መረጃ ከወቅቱ ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር እኩል ሲራመዱ ሳይ በጣም እቀናለሁ" ትላለች።

በ1902 ዓ.ም. "አዕምሮ" የተሰኘችው ጋዜጣ መታተም ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያን እየተፈራረቁ የመሯት መንግሥታት በብዙሃን መገናኛ በተለይ ደግሞ በህትመት ሚድያ ላይ የራሳቸውን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደሩ እሙን ነው።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል ኃላፊ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት በአሜሪካው 'ኒው ሜክሲኮ' ዩኒቨርሲቲ በተጋባዥ ፕሮፌሰርነት የሚያገለግሉት ዶ/ር አብዲሳ ዘርአይ እንደሚሉት "የህትመት ሚድያ ከኢህአዴግ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ያህል አዎንታዊ ለውጥ ቢያስመዘግብም አሁን ላይ ግን 'ለአደጋ የተጋለጠ' ሆኗል።"

ድህረ 97

ተከትለውት በመጡ ክስተቶች ዘወተር የሚወሳው የ1997ቱ ምርጫ በፕሬሱ ላይም ውጤቱ ጉልህ ነበረ። "ለእኔ ከ97ቱ ምርጫ በኋላ ያለው የህትመት ሚድያ የሞተ ነው" ሲል በቅርቡ ከእሥር የተለቀቀው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ይናገራል።

"ከምርጫው በኋላ በተለይ የግሉ ፕሬስ ከገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚደርስበት ጫና እጅግ እያየለ በመምጣቱ በርካታ የግል ጋዜጦች ከጨዋታ ውጭ ሊሆኑ ችለዋል" ይላል።

"ድህረ 97 መንግሥት የፀረ-ሽብር፣ የሲቪክ ማሕበረሰብ እንዲሁም የብዙሃን መገናኛን በተለመለከተ ባወጣቸው ህግጋት ብዙሃን መገናኛዎች ላይ ብርቱ ክንዱን ያሳረፈበት ጊዜ ነው" የሚሉት ደግሞ ዶክተር አብዲሳ ናቸው። "እነሆ ከዚያ ወቅት አንስቶ የግሉ ሚድያ በተለይ የህትመት ዘርፉ ማገገም አልቻለም።"

ለአምስት ዓመታት ያክል በየወሩ ሲታተም የቆየውና የአስቸኳይ ጊዜ ዘዋጁ መባቻ ላይ የተቋረጠው 'የአዲስ ስታንዳርድ' መፅሄት መሥራችና ዋና አዘጋጅ የሆነችው ጋዜጠኛ ፀዳለ ለማ መሰል ህግጋት የህትመት ሚድያው እንዲዳከም የበኩላቸውን እንደተጫወቱ ትስማማለች። "ህግጋቱ ካሳደሩብን ጫና አንፃር አንዳድንድ ጊዜ የትኛውን አትመን የትኛውን እንደምንተው ሁሉ አናውቀውም ነበር" ትላለች።

የቴክኖሎጂ ተፅዕኖ

አንዳንዶች የቴክኖሎጂው ዕድገት ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎችም ሃገራት ለህትመት ሚድያ መዳከም ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ሃሳባቸውን ይሰነዝራሉ።

"ሰዉ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ በግል ስልኩና በኮምፒውተር በቂ መረጃ ማግኘቱ ለህትመት ሚድያ መቀዛቀዝ ምክንያት ነው ብዬ አላምንም" ትላለች አልባብ። "እስቲ ያለሁበትን የናይሮቢ ከተማ ሁኔታ እንመልከት. . .ኬንያ በቴክኖሎጂ በተለይ በኢንተርኔት አቅርቦት ከኛ በጣም የላቀች ብትሆንም አሁንም ድረስ ዜጎቿ ጋዜጣ ሲያነቡ አያለሁ" ባይ ነች።

ጋዜጠኛ ፀዳለም ሆነ ተመስገን ደሣለኝ በአልባብ ሃሳብ ይስማማሉ። ሁለቱም የህትመት ሚድያው መዳከም ሰዉ ወደ በይነ-መረብ እንዲያጋድል አስገደደው እንጂ አሁንም የህትመት ውጤቶች አንባቢ ሞልቷል ይላሉ።

'የሆርን አፌይርሱ' ዳንኤል ብርሃነም ተመሳሳይ ሃሳብ አለው። "ሰው 'ከኦንላይን' የሚያገኘው መረጃ አርኪ ስለሆነ ነው ጋዜጦች እና መፅሔቶች ገዢ ያጡት ብዬ አላስብም። ሁኔታዎች ተመቻችተው የህትመት ውጤቶች አንጀት ላይ ጠብ የሚል ጉዳይ ይዘው ቢመጡ አንባቢ እንዳማያጡ እምነቴ ነው" ሲል ይደመጣል።

"ይልቁንስ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ የህትመት ሚድያ በኢትዮጵያ እጅግ ተዳክሟል" ይላል። "የፀረ ሽብር ህጉም በተወሰነ መልኩ ለዘርፉ መዳከም ሚና እንደተጫወተ አስባለሁ፣ ነገር ግን ህጉ አያስፈልግም ብዬ አላስብም" ሲል ይሞግታል።

ራስን ጠልፎ መጣል

ዶ/ር አብዲሳ የህትመት ሚድያ ዘርፍ አሁን ላጠላበት መቀዛቀዝ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ። "ከውስጣዊው ምክንያቶች አንዱ ከጋዜጠኞች ይታይ የነበረው ሙያዊ ሥነ-ምግባር ጉድለት ነው። አዲሱን ሥርዓት ለመጋፈጥ በሚል የተወለደው የግሉ ሚድያ ጅምላ ወቀሳ፣ ግጭት ቀስቃሽና ስም አጥፊ የሆኑ ይዘቶች ይታዩበት ነበር። ይህ ሁኔታ የግል ሚድያውን ራሱን ጠልፎ እንዲጥል ከማገዙም በላይ መንግሥት ጡጫውን እንዲያበረታ መንገድ ከፍቷል።"

"በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ላይ ሃገሪቱን የሚመራው መንግሥት የሚድያውን ባህርይ ባለመረዳቱ ምክንያት ዘርፉ እንዲያብብ ከማድረግ ይልቅ፤ በተቃራኒ እንደቆመ አካል ማየቱ ለህትመት ሚድያ ቁልቁለት መጓዝ እንደ ውጫዊ ምክንያት የሚጠቀስ ነው" ሲሉ ይተንትናሉ።

ነገር ግን የግሉ ህትመት ዘርፍ ራሱን ጠልፎ ሲጥል ወይም ከሙያ ሥነ-ምግባር ፈቀቅ ሲል "መንግሥት ክንዱን ከማፈርጠም ይልቅ በሌሎች ሃገራትም እንደሚሆነው በፕሬስ ካውንስል እንዲዳኝ ቢደረግ የት በደረስን" ባይ ናት ፀዳለ። ተመስገንም ቢሆን "የህትመት ዘርፉ ከጥፋት የፀዳ ባይሆን እንኳ ይህ ለመንግሥት ጡጫ መበርታት ምክንያት ሊሆን አይገባም" ይላል።

በ1999 ዓ.ም የተመሠረተው 'አዲስ ነገር' ጋዜጣ እስከ 30 ሺህ ኮፒ በመሸጥ በኢትዮጵያ የግል ህትመት ሚድያ ዘርፍ የጎላ እመርታ ማሳየት ከቻሉ ጋዜጣዎች አንዱ ነበር። ነገር ግን ከ2002 ምርጫ ጥቂት ወራት በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ከታተመ በኋላ አዘጋጆቹ ከመንግሥት ጫና ደርሶብናል በማለት ጋዜጣው መዘጋቱንና 'ፍርደ ገምድልነትን' በመፍራት ከሃገር መሸሻቸውን አሳወቁ።

በተመሳሳይ በርካታ አንባቢያን እንደነበሩት የሚታመነውና 'ፍትህ' ጋዜጣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ህልፈተ-ሕይወት ይፋ ከመሆኑ በፊት ሞታቸውን የተመለከተ ዜና በመሥራቱ ምክንያት ወደ 30 ሺህ የሚደርስ ዕትም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲቃጠል ከተደረገ በኋላ ከገበያ ውጭ እንደሆነ አዘጋጁ ተመስገን ደሳለኝ ያስታውሳል።

ዕለታዊ አዲስ፣ ኢትኦጵ፣ ሞገድ፣ ልሳነ-ሕዝብ፣ ምኒልክ፣ ጦቢያ፣ ሳተናው፣ ነፃነት፣ አውራንባ ታይምስ፣ መብረቅ፣ ሰይፈ ነበልባል፣ ፍትህ፣ ፋክት፣ አዲስ ታይምስ፣ አዲስ ነገር. . . ከብዙ በጥቂቱ አንድ ሰሞን ብቅ ብለው የጠፉ የህትመት ውጤቶች ናቸው።

ወደፊት. . .?

ከእነዚህ የህትመት ውጤቶች በኋላ በኢትዮጵያ ይሄ ነው የሚባል በተለይ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ የሚሠራና በግሉ ዘርፍ የሚተዳደር ጋዜጣም ሆነ መፅሔት አልተስተዋለም። ፎርቹን፣ ሪፖርተርና አዲስ አድማስን የመሳሰሉ ጋዜጦች በገበያው ላይ መቆየት ቢችሉም ጠንካራ የሚባል ፖለቲካዊ ዕይታ የሚንፀባርቅባቸው ግን አይደሉም ስትል ፀዳለ ትሞግታለች።

አዲስ ስታንዳርድ በአሁኑ ወቅት በድረ-ገፅ ይዘቱን የሚያሰራጭ ሲሆን "ሁኔታው ቢመቻችልን ወደ ህትመት የማንመልስበት ምንም ምክንያት የለም" ትላለች ዋና አዘጋጇ። "መንግሥት በመጀመሪያ ደረጃ ዘርፉን ጠፍረው የያዙትን ህግጋት ማሻሻል አለበት። ጋዜጠኞች የሽብር ወንጀል በመፈፀም ከተጠረጠሩ ግለሰቦች እኩል የሚዳኙበት ሃገር ላይ ነው ያለነው። ከዚያም አልፎ መንግሥት ራሱን በሚድያ ፉክክር ውስጥ ማስገባቱ ሌላኛው ትልቅ ፈተና ነው።"

እንደ ዶ/ር አብዲሳ ከሆነ "ለመንግሥት 'ብዝሃነት' ማለት ከብሔር ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው። ነገር ግን ብዝሃነት ከአስተሳሰብና ፍልስፍና ጋር ትልቅ ቁርኝት ያለው ነገር ነው። ሚድያውን እንደ ባላጋራ ከማየት ይልቅ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ማገዝ አስፈላጊ ነው።"

ስለዚህ መንግሥት የግሉን ህትመት ሚድያ አላንቀሳቅስ ያሉትን ሕጋዊና አስተዳደራዊ እንቅፋቶችን ለማስወገድ ያለው ዝግጁነትና የሃሳብ ልዩነትን ለማስተናገድ ፈቃደኛ መሆኑን ማሳየት የብዙዎች ጥያቄ ነው።

"መቼ ይሆን የሃገሬ ሰዎች እንደልባቸው ጋዜጣ እያገላበጡ ወደ የፊናቸው ሲያመሩ የማየው?" ብላ የምትጠይቀው ደግሞ አልባብ ናት።