ስለ አንጀታችን የማያውቋቸው ስድስት አስገራሚ እውነታዎች

የአንጀት ስዕል

የፎቶው ባለመብት, BSIP

ሁሉንም የሚያከናውናቸውን ሥራዎች ያለ ማንም ትዕዛዝ የሚፈጽመውና ለአጠቃላይ ጤናችን ከፍተኛ ሚና የሚጫወተው አንጀታችን በብዙዎች 'ሁለተኛው አንጎል' በመባል ይጠራል።

የዘርፉ ተመራማሪዎች እንደሚሉት አንጀታችን ምግብ ከመፍጨት የበለጠ ሌሎች ብዙ ነገሮችን ያከናውናል።

ዶክተሮች እንዲውም አንጀት የአእምሮ ህመምን ለማከምና የሰዎችን በሽታ የመከላከል አቅም ለመገንባት የሚያደርገውን አስተዋጽ በግልጽ ለመለየት ምርምር ጀምረዋል።

በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ቢቢሲ ያነጋገራቸው አውስትራሊያዊቷ ሜጋን ሮሲ በአንጀት ጤናና ህክምና ላይ በተለይ የሚሰሩ ዶክተር ናቸው። ስለምንበላቸው ምግቦችና በአንጀታችን ዙሪያ ማወቅ ስላሉብን ስድስት እውነታዎች ነግረውናል።

1. ራስ ገዝ የነርቭ ሥርዓት

ከሌሎቹ የሰውነት ክፍሎቻችን በተለየ መልኩ አንጀታችን በራሱ ጊዜ የሚያደርጋቸው ነገሮች ብዙ ናቸው። ማንኛውንም አይነት ትእዛዝ ከአንጎላችን እስኪመጣ አይጠብቅም።

አንጀታችንን የሚያዘው አንጎላችን ሳይሆን ''ኢንትሪክ የነርቭ ሥርዓት'' የሚባለው ሲሆን፤ ይህም በዋነኛነት የሚቆጣጠረው ከሥርዓተ-ልመት (የምግብ መፈጨትና መዋሃድ) ጋር የተያያዙ ሂደቶችን ነው።

ምንም እነኳን አንጀታችን ነገሮችን በራሱ ቢያናከውንም፤ ከማዕከላዊው የነርቭ ሥርዓት ጋር ግን መረጃዎችን ይለዋወጣል።

2. 70 በመቶ የሚሆኑት የሰውነታችን በሽታ ተከላካይ ሴሎች በአንጀታችን ውስጥ ይገኛሉ

እንደ ዶክተር ሮሲ ከሆነ ይህ እውነታ አንጀታችን ከበሽታ መከላከልና ከአጠቃላይ ጤንነታችን ጋር በጥብቅ የተቆራኘ እንዲሆን ያደርገዋል።

ተመራማሪዎች እንደሚሉት የአንጀት ህምም ባጋጠመን ጊዜ እንደ ጉንፋን ላሉ በሽታዎች በቀላሉ ተጋላጭ እንሆናለን።

3. 50 በመቶ የሚሆነው የሰዎች አይነምድር ባክቴሪያ ነው

ግማሽ ያህሉ ከሰውነታችን የሚወደው አይነ ምድር ባክቴሪያ ቢሆንም፤ አብዛኞቹ ባክቴሪያዎች ግን ጎጂ አይደሉም። ጎጂ ቢሆኑ እንኳን የአንጀታችን የመከላከል ብቃት ከፍተኛ ስለሆነ ብዙም የሚያሳስብ አይደለም።

ነገር ግን ይላሉ ዶክተር ሮሲ አንጀታችንን ሥራ ካበዛንበትና ካልተንከባከብነው ውጤቱ አስከፊ ሊሆን ይችላል። ማንኛውም ሰው በቀን ቢያንስ ሦስት ጊዜ ወደ መጸዳጃ ቤት ጎራ ቢል መልካም ነው ባይ ናቸው።

የተለያዩ አትክልቶች

የፎቶው ባለመብት, Thinkstock

4. የተለያዩ አይነት ምግቦች ስንመገብ አንጀታችን ደስ ይለዋል

አንጀታችን ውስጥ በትሪሊዮኖች የሚቆዎጠሩና ብዙ ጥቅም ያላቸው "ማይክሮብስ" የሚባሉ ጥቃቅን ነገሮች ያሉ ሲሆን እነሱ ደግሞ የተለያየ አይነት ምግቦች ወደ አንጀታችን ሲገባ የሥራ ፍጥነታቸው ይጨምራል።

እነዚህ ማይክሮብ የተባሉት ነገሮች የሥርዓተ ልመቱን ከማፋጠን አልፎ በምግቦች ውስጥ ያለውን ውሃ ለመምጠጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

''ማይክሮብስ'' በቤታችን እንደሚገኙ የቤት እንስሳት እንደማለት ናቸው። የእኛን እንክብካቤ ይፈልጋሉ በማለት ገልጸዋቸዋል ዶክተር ሮሲ።

5. የሆድ እቃችን ከጭንቀትና ስሜቶቻችን ጋር ግንኙነት አለው

ከሆድና አንጀታችን ጋር የተገናኘ ማንኛውም አይነት ህመም ሲሰማን መጀመሪያ ልናስበው የሚገባው ነገር በሰዓቱ ጭንቀት ውስጥ መሆን አለመሆናችንን ነው።

ለዚህም ነው በቅርቡ እየተሞከሩ ባሉ አዳዲስ የህክምና አይነቶች የአእምሮ በሽታና ቀላል ጭንቀቶችን ለማከም ጎጂ ያልሆኑ ባክቴሪያዎችን ወደ አንጀት ማስገባት የተጀመረው።

የዘርፉ ባለሙያዎች እያደረጉት ባለው ጥናት ጤናማ የሆነ አንጀት ያላቸው ሰዎች ጤናማ ካልሆነ አንጀት ካላቸው ጋር ሲወዳደሩ ለጭንቀትና ሌሎች የአእምሮ በሽታዎች ያላቸው ተጋላጭነት የቀነሰ ነው።

6. የአንጀትዎትንና የሥርዓተ-ልመት ሂደቶችን ለማስተካከል የሚከተሉትን ያድርጉ

  • የተለያዩ የምግብ አይነቶችን ይመገቡ
  • ጭንቀት ይቀንሱ
  • የሰውነት እንቅስቃሴ ያድርጉ
  • የአንጀት ህመም ካለብዎት የአልኮል መጠጦችን፣ ቡና እንዲሁም ቅመም የበዛባቸው ምግቦች አያዘውትሩ
  • ረጅምና ያልተቆራረጠ እንቅልፍ ያግኙ