ሃሰተኛ የመዋቢያ ምርቶች መርዛማ ንጥረ-ነገሮችን ይዘው ተገኙ

ሃሰተኛ የመዋቢያ ምርቶች

የፎቶው ባለመብት, Local Government Association

ሜርኩሪን የመሳሰሉ መርዛማ ንጥረ-ነገሮች በሃሰተኛ የመዋቢያ ምርቶች ውስጥ ተገኙ።

የእንግሊዝ የአካባቢ ባለስልጣናት ማህበር ከሆነ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ፓዎንድ ሊያወጡ የሚችሉ ሃሰተኛ የመዋቢያ ምርቶች ገበያ ላይ መኖራቸውን ደርሼበታለው ብሏል።

ማህበሩ ጨምሮ እንዳለው ምርቶቹ ''ከፍተኛ የሆነ የጤና መታወክ ያስከትላሉ'' እንዲሁም የአምራቾች ንግድ ይጎዳሉ፤ ተጠቃሚዎችንም ያሳስታሉ።

ሃሰተኝ ምርቶቹ ታዋቂ የሆኑ እንደ ማክ፣ ሽኔል እና ቤኔፊት የተሰኙ ምርቶችን ስም እና መልክ ይዘው ይወጣሉ።

ማህበሩ ሃሰተኛ ምርቶቹ የያዟቸው አደገኛ ምርቶች በቆዳ ላይ ጉዳት ያደርሳሉ ብሏል።

ቆዳ ላይ ከሚያደርሱት ጉዳት በተጨማሪ፤ ''በስርዓተ-ልመት፣ በሳምባ፣ በኩላሊት፣ በዓይን እና በበሽታ የመከላከል ስርዓት አቅማችን ላይ ጉዳት ያስከትላሉ።"

በቅርቡ የተያዙ ሃሰተኛ ምርቶች በውስጣቸው ሜርኩሪ እና ከፍተኛ መጠን ያለው ቆዳን ለማንጣት ጥቅም ላይ የሚውል ሃይድሮኩኢኖን የተሰኙ ንጥረ-ነገሮች ተገኝተዋል።

የማህበሩ ሰብሳቢ ሳይመን ብላክበርን ''ከምንም በላይ የመዋቢያ ምርቶችን ከመግዛታችን በፊት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ምርቶቹን ለገብያ ያቀረበው ሻጭ ማን እንደሆነ ለማጣራት እንሞክር። ዘወትር ማስታወስ ያለብን አንድ የመዋቢያ ምርት ዋጋው ከተለመደው ዝቅተኛ ከሆነ ሃሰተኛ ሊሆን ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል'' ብለዋል።