ደቡብ ሱዳን በናይል ወንዝ ላይ የመጀመሪያውን ቋሚ ድልድይ አስመረቀች

የተሰራው ድልድይ

የፎቶው ባለመብት, Nichola Mandi

ደቡብ ሱዳን በናይል ወንዝ ላይ የሰራችው የመጀመሪያው ቋሚ ድልድይ ሀሙስ እለት ግንቦት 11፣ 2014 ዓ.ም በይፋ ተመርቋል።

በርካታ ህዝብም ደስታ በተቀላቀለበት ስሜት ድልድዩንም ለማቋረጥ ወጥቷል።

በዋና ከተማዋ ጁባ ጠርዝ ላይ የሚገኘውና 560 ሜትር ርዝመት ያለው የነጻነት ድልድይ ( ፍሪደም ብሪጅ) የተገነባው ከጃፓን መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ነው።

ግንባታው የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 2013 ቢሆንም በእርስ በርስ ጦርነት እና በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በተደጋጋሚ ተቋርጦ ነበር።

ከዚህ ቀደም የነበረው ጊዜያዊ ድልድይ ከአካባቢው የተነሳ ሲሆን በተለይ ለእግረኞች ለመሻገር አደገኛ ነበርም ተብሏል። ድልድዩም እንዲፈርስ እንደሚደረግም ተገልጿል።

የድልድዩ የምርቃት ስነ ስርዓት ላይ የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ እጩ እና የአፍሪካ ህብረት የመሠረተ ልማት ልዑክ ራይላ ኦዲንጋ እንዲሁም የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ኃላፊ ታናካ አኪሂኮ ተገኝተዋል።

የነጻነት ድልድይ በጃፓን እና በደቡብ ሱዳን ህዝቦች መካከል የረጅም ጊዜ እና ዘላቂ ወዳጅነት ምልክት መሆኑን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ለተሰበሰበው ህዝብ ተናግረዋል።

ድልድዩ በጁባ ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ ከማቃለሉም በላይ ንግዱን ለማሳለጥ ይረዳል ተብሎ ይጠበቃል።