ማንቸስተር ሲቲ ከሊቨርፑል፡ ስለኃያላኑ ፍልሚያ ማወቅ የሚገባዎ

እሑድ አመሻሹን ማንቸስተር ሲቲ ከሊቨርፑል በኤቲሃድ ስታድዬም ተገናኝተው የውድድሩን ዘመኑን ትልቁን ፍልሚያ ያደርጋሉ።

ጨዋታው ዋንጫው ወዴት ሊሄድ እንደሚችልም ጠቋሚ ነው።

የፔፕ ጉዋርዲዮላ ቡድን በ73 ነጥብ ሊጉን ይመራል። ቀያዮቹ የዩርገን ክሎፕ ልጆች ደግሞ በአንድ ነጥብ ይከተላሉ።

የዘንድሮው ፕሪሚዬር ሊግ ሊገባደድ ሰባት ከዛሬው ፍልሚያ በኋላ ሰባት ጨዋታዎች ይቀራሉ።

ሊቨርፑል ያለፉትን 10 ጨዋታዎች አሸንፏል። ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች አምስት ነጥብ ጥሏል።

ሊቨርፑል ይህን ጨዋታ ከረታ ከጥቅምት አንድ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊጉን ይመራል።

ሁለቱ ቡድኖች ባለፉት ስምንት የፕሪሚዬር ሊግ ዘመናት 10 ጨዋታ እየቀረ ተገናኝተው ሰባት ጊዜ የረታው ሁለተኛ ያለው ቡድን ነው።

ካራባዎ ዋንጫን ያነሱት ሊቨርፑሎች አራት ዋንጫ በማንሳት ታሪክ ሊሠሩ ይችላሉ።

ሲቲዎች ደግሞ ፕሪሚዬር ሊጉን፣ ቻምፒዮንስ ሊግና ኤፍ ኤ ዋንጫን ለማንሳት ይፋለማሉ።

ዩርገን ክሎፕ ይህ ጨዋታ በጣም ወሳኝ እንደሆነ ነጋሪ እንደማያስፈልገው በጋዜጣዊ መግለጫቸው አውስተዋል።

ጉዋርዲዮላ ደግሞ ሊቨርፑል በማጥቃት ሊበልጠን ቢችልም በብዙ ነገር ተመሳሳይነት አለን ሲሉ ተደምጠዋል።

ሁለቱ ቡድኖች በዚህ የውድድር ዘመን 147 ጎሎች አስቆጥረዋል። ሊቨርፑል በሰባት ጎሎች በልጦ የመጀመሪያውን ሥፍራ ይዟል።

የእግር ኳስ መረጃ ሰብሳቢው ኒዬልሰን ግሬስኖት ሲቲ ይህን ጨዋታ ከረታ ዋንጫውን የማንሳት ዕድሉ 86 በመቶ ከፍ ይላል፤ ሊቨርፑል ከረታ ደግሞ 68 በመቶ ተስፋ ይኖረዋል ይላል።

ማንቸስተር ሲቲ ካይል ዎከርና ፊል ፎደንን በሙሉ አቋማቸው ሊያሰልፋቸው ይችላል።

ወጣቱ ፎደን ሲቲ ከሊቨርፑል ባደረጋቸው ያለፉት ሶስት ጨዋታዎች ጎል ማስቆጠር ችሏል። ዛሬ አንድ ጎል ካከለ ከጄሚ ቫርዲ ቀጥሎ ቀያዮቹ ላይ በተከታታይ ያስቆጠረ ተጫዋች ይሆናል።

ክሎፕ በሊቨርፑል በኩል አዲስ የተጎዳ ተጫዋች እንሌለ ገልጠዋል።

የ14 ነጥብ ልዩነት የሃሰት ነበር

ከፈረንጆቹ 2018/19 የውድድር ዘመን ጀምሮ ሁለቱ ቡድኖች 144 ጨዋታዎች አድርገው ሲቲ 338 ነጥብ ሲሰበስብ ሊቨርፑል ደግሞ 337 ይዟል።

ባለፈው ጥር ሲቲ በኬቪን ደ ብራይን ጎል በርንሊ አንድ ለዜሮ ሲረታ ብዙዎች ዋንጫው ወደ ኤቲሃድ አመራ ብለው ነበር።

በወቅቱ ማንቸስተር ሲቲዎች ከሊቨርፑል ጋር የነበራቸው የነጥብ ልዩነት 14 ነበር።

ሊቨርፑል በዚህ ጊዜ ከቶተንሃም አቻ በመውጣት በሌይስተር በመረታት ቀጥሎ ከቼልሲ ነጥብ በመጋራት የዋንጫ ተስፋቸውን ያጨለሙ መሰሉ።

ሲቲ በበኩሉ ከሳውዝሃምፕተንና ፓላስ አቻ ሲወጣ በቶተንሃም ተረታ።

የ14 ነጥብ ልዩነት የት ገባ ተብለው የተጠየቁት ጉዋርዲዮላ "ልዩነቱ የሃሰት ነበር" ሲሉ መልሰዋል።

ሊቨርፑል የትኛውም የእንግሊዝ ቡድን አድርጎት የማያውቀውን በአንድ ዓመት አራት ዋንጫ የመብላት ሕልማቸውን ለማሳካት ይፋለማሉ።

በኤፍ ኤ ዋንጫ ድጋሚ ሊቨርፑልና ሲቲ በሚቀጥለው ቅዳሜ ይገናኛሉ። ይህ ማለት ከሁለቱ ቡድኖች አንዱ ኤፍ ኤን የማንሳት ሕልሙ ይከስማል ማለት ነው።

ነገር ግን ለፔፕ ጉዋርዲዮላ ከምንም በላይ የቻምፒዬንስ ሊግ ዋንጫን ማንሳት ይቀድማል።

ፔፕና ክሎፕ በጀርመን ቡንደስሊጋንና በፕሪሚዬር ሊጉ 22 ጊዜ ተገናኝተዋል። ዘጠኝ ጊዜ ክሎፕ ሲረቱ አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።

ሲቲ ባለፉት 11 ጨዋታዎች ሊቨርፑልን ገጥሞ ጎል ሳይቆጥር የወጣበት ጨዋታ የለም።

ሁለቱ ኃያላን ቡድኖች ዛሬ አመሻሹን ድጋሚ ይገናኛሉ። ማን ይረታ ይሆን? ጊዜ ይፈታዋል።