ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ከተሞች የተካሄዱ ውድድሮችን አሸነፉ

የፓሪስ ማራቶን አሸናፊው አትሌት ጫሉ ዴሶ ገልሜሳ

የፎቶው ባለመብት, FRANCK FIFE

የምስሉ መግለጫ, የፓሪስ ማራቶን አሸናፊው አትሌት ጫሉ ዴሶ ገልሜሳ

በሳምንቱ መጨረሻ በተካሄዱ የተለያዩ የማራቶን ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸናፊ ሆነዋል።

በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድር በወንዶች ምድብ ኢትዮጵያዊው አትሌት ጫሉ ዴሶ ገልሜሳ ውድድሩን በ2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ7 ሰከንድ በሆነ ሰዓት በማጠናቀቅ አሸናፊ መሆን ችሏል።

አትሌቱ ሰይፉ ቱራ ደግሞ 2ኛ ሆኖ በማጠናቀቅ በፓሪሱ ማራቶን የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል።

በሴቶች ምድብ ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፋንቱ ጂማ የቦታውን ሪከርድ ያሻሻለችውን ኬንያዊቷን አትሌት ጁዲት ጄፕቱምን ተከትላ በመግባት የብር ሜዳሊያ ስታሸንፍ አትሌት በሱ ሳዶ ደግሞ ውድድሩን በሦስተኝነት በማጠቀቅ የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች።

ስፔን ባርሴሎና ውስጥ በተደረገ የወንዶች ግማሽ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊው አትሌት ሐፍቱ ተክሉ እና አትሌት ጫላ ረጋሳ አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው በመጨረስ የወርቅ እና የብር ሜዳሊያውን ወስደዋል።

በተመሳሳይ በሴቶች ምድብ የግማሽ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጌጤ ዓለማየሁ ሁለተኛ፣ አትሌት አስናቀች አወቀ ሶስተኛ እና አትሌት ረድኤት ዳንኤል ደግሞ አራተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በሌላ ውድድር በ2022 የኮሪያ ዴጉ ዓለም አቀፍ ማራቶን ኢትዮጵያዊው አትሌት ሽፈራው ታምሩ 2:06:31 በሆነ ሰዓት አንደኛ በመውጣት አሸንፏል።

በሴቶች ዴጉ ዓለም አቀፍ ማራቶን ኤርትራዊቷ ናዝሬት ወልዱ አሸናፊ ሆናለች።

በጣልያን በተካሄደው የሚላኖ 2022 ማራቶን ውድድርም ኢትዮጵይውያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል።

በሴቶች ምድብ አትሌት ስንታዬሁ ጥላሁን 2ኛ ሆና ስታጠናቅቅ ሌላኛዋ የአገሯ ልጅ አትሌት አታለል አንሙት የ3ኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች። ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ያለውን ደረጃም ቢሆን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው የያዙት።