የዮርዳኖሱ ልዑል ሐምዛ ቢን ሁሴን ልዑልነት በቃኝ አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዮርዳኖስ አልጋ ወራሽ የነበሩት ልዑል ሐምዛ ቢን ሁሴን ልዑልነት በቃኝ አሉ።
ልዑል ሐምዛ "የግል አመላካከቴ ከዘመናዊ ተቋሞች" ጋር አይጣጣምም ብለዋል።
ልዑሉ የሟቹ ንጉስ ሁሴን አራተኛ ልጅ እና የአሁኑ ንጉስ አብዱላህ ታናሽ ወንድም ናቸው።
ባለፈው ዓመት የሃገሪቱን መሪዎችን በሙስና እና በአቅም ማነስ ከተቹ በኋላ ለቁም እስር ተዳርገው ነበር።
በሐምዛ የተፈረመ እና ወንድማቸው ንጉስ አብዱላህን ይቅርታ ጠይቀውበታል የተባለለት ወረቀት በመጋቢት ወር በዮርዳኖስ መንግስት ይፋ ተድርጓል።
ሃምዛ በትዊተራቸው ላይ በለጠፉት መግለጫ "በቅርብ ዓመታት የተመለከትኩት አባቴ በውስጤ ካሰረፀው የግል እምነቴ ጋር የማይጣጣም ነው። በሕይወቴ ጠንክሬ አሳካዋለሁ ብዬ የሞከርኩት ከተቋሞቻችን አሠራሮች እና ዘመናዊ አካሄዶች ጋር ባለመጣጣማቸው እዚህ መደምደሚያ ላይ ደርሻለሁ።"
"ከታማኝነት፣ ከፈጣሪ እና ከህሊና አንጻር ሳየው የልዑልነት ማዕረጌን ገሸሽ ከማድረግ እና ከመተው በቀር ምንም ነገር አይታየኝም። በሕይወቴ ለዓመታት የምወዳትን ሃገሬን እና የምወደውን ህዝቤን በማገልገል ትልቅ ክብር ይሰማኛል።"
"በህይወት እስካለሁ ድረስ እንደዚህ በፊቱ ለምወዳት ዮርዳኖስ ታማኝ ሆኜ እኖራለሁ" ብለዋል።
ልዑል ሐምዛ ማን ናቸው?
ልዑል ሃምዛ የሟቹ ንጉስ ሁሴን እና የተወዳጅ ሚስታቸው የነበሩት ንግሥት ኑር የበኩር ልጅ ናቸው። ልዑሉ ከእንግሊዝ ሃሮው ትምህርት ቤት እና ከሮያል ወታደራዊ አካዳሚ ተመርቀዋል። ከአሜሪካ ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲም ተምረዋል። በኋላም በዮርዳኖስ የጦር ኃይሎች ውስጥ አገልግለዋል።
እአእ በ1999 የዮርዳኖስ ልዑል ተብለው ተሰይመዋል። የንጉስ ሁሴን ተወዳጅ ልጅ የነበሩ ሲሆን ንጉሱ በአደባባይ ጭምር "የዓይኔ ደስታ" ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
ንጉስ ሁሴን በሕይወት ሲለዩ ንጉስነቱን እንዳይረከቡ በጣም ወጣት እና ልምድ የሌላቸው ሆነው ታይተዋል።
በምትኩ ታላቅ ወንድማቸው አብዱላህ ዙፋኑን ተረክበዋል። በኋላም ሃምዛን የዘውድ ልዑልነት በ2004 ገፈፉ።
የዮርዳኖስን መሪዎችን በሙስና እና በብቃት ማነስ ከከሰሱ በኋላ እአአ ሚያዝያ 2021 ሃምዛ የቁም እስረኛ መደረጋቸውን ባሰራጩት ቪዲዮ ይፋ አድርገዋል።
ይህ የሆነው ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ በርካታ ከፍተኛ አመራሮች ከታሰሩ በኋላ ነው።
ልዑል ሐምዛህ ምንም አይነት ጥፋት እንዳልፈፀሙ እና የየትኛውም ሴራ አካል እንዳልነበሩ ተናግረዋል።
የዮርዳኖስ ጦር ሃምዛ በቁም እስር ላይ መሆናቸውን አስተባብሏል። ይሁን እንጂ ልዑሉ የዮርዳኖስን "ደህንነት እና መረጋጋት" አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ድርጊቶችን እንዲታቀቡ መታዘዛቸውን ገልጸዋል።
ንጉስ አብዱላህ በኋላ በቴሌቭዥን ቀርበው ሃምዛ "ከቤተሰቦቹ ጋር በቤተ መንግስቱ ውስጥ በኔ ጥበቃ ስር ነው" ብለዋል።
ልዑል ሐምዛ ከዚያ ወዲህ በአደባባይ ብዙም አይታዩም ነበር። መጋቢት ላይ ደግሞ የዮርዳኖስ ንጉሣዊ ፍርድ ቤት ሃምዛ ለወንድማቸው የጻፉትን ደብዳቤ ይፋ አድርጓል።
"ባለፈው ዓመት ውዷ ሃገራችን ዮርዳኖስ ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁማለች። በታሪኳም አሳዛኝ ምዕራፍ ነበር" ይላል ደብዳቤው።
"ግርማዊነትዎ ተሳስቻለሁ። ሰው ደግሞ ይሳሳታል። ስለዚህ ባለፉት ዓመታት በግርማዊነትዎ እና በሃገራችን ላይ ለፈፀምኳቸው ጥፋቶችና የሁከት ክስተቶች ለደረስኩባቸው ሁኔታ ተጠያቂ ነኝ።" ይላል ደብደባው።












