እንደ ስቲቭ ጆብስ ያሉ ባለራዕዮች ጥሩ መሪ ናቸውን?

ስቲቭ ጆብስ

የፎቶው ባለመብት, Justin Sullivan

የምስሉ መግለጫ, ስቲቭ ጆብስ

ስቲቭ ጆብስ አፕል የተሰኘውን ስልክ ለገበያ በማቅረብ ዓለምን ከቀየሩ ሰዎች የሚቀመጥ ነው። ነገር ግን ስቲቭ ጆብስ በስሩ የነበሩ ሠራተኞቹን በአግባቡ ያዳምጥ ነበር?

ሌላኛዋ ባለራዕይ ሮዚ ጊንዴይ ማካሩን የተሰኘውን ጣፋጭ ምግብ በመሥራት የበርካታ ታዳጊዎችን ሕይወት መንካት ችላለች። የእነዚህን ሁለት ባለራዕዮች ሕይወት እንዳስሳለን።

ስቲቭ ጆብስ

ፈር ቀዳጅ፣ ሥራ ፈጣሪ እንዲሁም ባለ ምጡቅ አእምሮ የሚሉ ስያሜዎች ተሰጥተውታል ይህ ግለሰብ። በቴክኖሎጂው ዘርፍ በርካታ አስተሳሰቦችን የቀየረና ብዙ ነገሮችን ያበረከተ ነው ስቲቭ ጆብስ።

ከጓደኛው ስቲቭ ዎዝኒያክ ጋር በመሆን በአውሮፓውያኑ በ1970ዎቹ የቤተሰቦቹ መኪና ማሳደሪያ ቤት ውስጥ የጀመሩት ሥራ አሁን ከዓለማችን ትልልቅ ድርጅቶች መካከል ለመሆን በቅቷል።

ከዓመታት በኋላ ማክንታሽ የተባለውን ኮምፒውተር ለገበያ ያቀረቡ ሲሆን በመቀጠል አይፓድ እንዲሁም አይፎንን አስተዋውቋል።

ስቲቭ ጆብስ ያስተዋወቀው ምርት የበርካቶች መነጋገሪያ ሆነ። ሰዎችን የማሳመን ብቃቱ እና የሥራ ፍቅሩ በብዙዎች ዘንድ ክብርን አስገኝቶለታል።

በአፕል ስር የሚተዳደረውና የአፕል ምርቶች ላይ ብቻ የሚሠራው አይቱንስ የተሰኘው የሙዚቃ ማዳመጫ በዓለማችን ትልቁ እንደሆነ ይነገርለታል።

ነገር ግን ስቲቭ ጆብስ ከእነዚህ አስደናቂ ስኬታማ ባህሪዎቹ በዘለለ ሰዎችን አጥብቆ መቆጣጠር የሚወድና ወግ አጥባቂ የሚባል እንደሆነ ብዙዎች ይመሰክራሉ።

ስቲቭ ጆብስ ሠራተኞቹን በሰዎች ፊት ያዋርድና ተገቢ ያልሆኑ ንግግሮችን ይናገር እንደነበር እንዲሁም በጣም ከባድ የሆኑ ትእዛዞችን ያስተላልፍ እንደነበር ሠራተኞቹ ይገልጻሉ።

ምንም እንኳን መብታችንን አናስነካም ያሉ አንዳንድ ሠራተኞች በስቲቭ ጆብስ ዘንድ ክብርን ማግኘት ቢችሉም በርካታ ባለተሰጥኦ ሠራተኞቹ ግን ሥራቸውን ለቅቀው ለመሄድ ተገደዋል።

የስቲቭ ጆብስ የአመራር መንገድ የተለመደ ባይሆንም በርካታ ባለራዕዮች የሚጋሩት ይመስላል።

ስቲቭ ጆብስ በስሩ የሚገኙ ሠራተኞቹን ማድመጥ አይፈልግም ነበር። በጣም ጠንካራ የሆኑ ሐሳቦች የነበሩት ሲሆን የሌሎችን አስተያየት ግን ለመስማት እምብዛም ፈቃደኛ አይደለም።

እንኳን ደንበኛ ክርክር አይደለም በጉዳዮች ዙሪያ ከስቲቭ ጋር ሐሳብ መለዋወጥ በጣም ከባድ ነው።

ሁሌም ቢሆን እሱ የፈለገው እንዲሆንና የእሱ ሐሳብ ብቻ እንዲደመጥ ነበር የሚፈልገው። ነገር ግን ይህ ባህሪ ለሠራተኞቹ ምን ማለት ነው?

በተግባር እንደ ስቲቭ ጆብስ ካሉ ባለራዕዮች ጋር መሥራት ማለት ምንም ዓይነት ጥያቄ ሳይጠይቁ የተባሉትን ነገር መሥራት ማለት ሊሆን ይችላል።

በኅብረት ንግግር ላይ ተመሥርቶ የሚሠራ ነገር የለም። ሐሳብ ይመጣል፣ ሠራተኞቹ በተባሉት መንገድ ተግባራዊ ያደርጉታል።

አንድ መሪ ብቻ ነው ያለው። መሪውም ግልጽ የሆነ ራዕይ ያለው ሲሆን በምንም ዓይነት ሁኔታ የሌሎችን ሰዎች ሐሳብ ለመስማት ፍላጎት የለውም።

ሠራተኞች የባለራዕዩን ሐሳቦች ተግባራዊ ማድረግ ካልቻሉ የራሳቸው ችግር ነው። ችግሩ ከሠራተኞቹ እንጂ ከሐሳቡ አልያም ከባለራዕዩ ሊሆን እንደሚችል አይታሰብም።

እንደ ስቲቭ ጆብስ ያሉ ባለራዕዮች ከሰዎች ጋር ተስማምተው መሥራት ካልቻሉና የሰዎችን ሐሳብ ለማድመጥ ፈቃደኛ ካልሆኑ እነሱን ገሸሽ ማድረግ ይቻላል?

መሰል የአመራር ሂደቶች በርካቶችን ለተሻለ ነገር የሚያነሳሱ ቢሆንም በሂደቱ ግን በርካቶች ደስተኞች አይሆኑም።

መሪዎች ሲባሉ ሁሌም ቢሆን በስራቸው ያሉ ሰዎች በማንኛውም አይነት ሁኔታ ሊከተሏቸውና ሊያምኗቸው እንደሚገባ ይነገራል።

በሌላ በኩል ደግሞ ባለራዕይ መሪዎች ሁሌም ቢሆን ያሰቡትን ለማሳካት የማይፈነቅሉት ድንጋይ ስለማይኖር ከነሱ ለመማር ዝግጁ የሆነ ሰው ብዙ ነገሮችን ሊያተርፍ ይችላል።

ነገር ግን የእኔ ሐሳቦችና አስተያየቶች ለምን አይደመጡም? ብሎም ቅሬታ ውስጥ አይገባም።

ስለዚህ በነዚህ የአመራር መንገዶች መካከል ግልጽ የሆነ ይሄኛው ትክክል ሌላኛው ደግሞ ስህተት የሚባል ነገር የለም።

ግልጽ የሆነ ራዕይ ያለው መሪ በርካቶችን ሊያነሳሳ ይችላል። ነገር ግን በነሱ ራዕይ ሁሉም ሰው ሊስማማና ሊያምንበት ይገባል።

በሌላ በኩል ባለራዕይ መሪዎች ያሰቡትን ለማሳካት በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ የሌሎች ሰዎች ሐሳብ ቢደፈጠጥ አልያም የሰዎች ስሜት ቢጎዳ ብዙም አያሳስባቸውም። ዋናው ነገር ከግብ መድረስ ብቻ ነው።

ስለዚህ ለባለራዕይ መሪዎች እንደ ምክር የሚቀመጥ ነገር ቢኖር ሁሌም ቢሆን የራሳችሁን ሐሳብ ብቻ አታስቀድሙ። ሁሉም ነገር ስለእነሱ እንዳልሆነ ሊረዱም ይገባል።

ሮዚ ጊንዴይ

እንግሊዝ በርሚንግሀም ውስጥ ሚስ ማካሩን የተባለ ድርጅት የመሠረተችው ሮዚ በጣም ጣፋጭና ከፍተኛ ተወዳጅነትን ማትረፍ የቻሉ ምግቦችን በዋነኛነት ታመርታለች።

ነገር ግን ድርጅቱ የሚያመርታቸው ጣፋጭ ብስኩቶች ብቻ አይደሉም ይህንን ድርጅት ለየት የሚያደርጉት።

በድርጅቱ ተቀጥረው እነዚህን ጣፋጭ ብስኩቶች የሚያመርቱት በአካባቢው አስቸጋሪ ሕይወት ውስጥ የነበሩ ወጣቶች መሆናቸው ነው።

ሮዚ እንደምትለው የንግድ ሥራዋ ማኅበረሰቡ ላይ ያተኮረና የተመሠረተ ነው። ወጣት ሠራተኞቿንም በራሳቸው እንዲተማመኑና የፈለጉትን ነገር ማድረግ እንዲችሉ ትረዳቸዋለች።

የሮዚ ራዕይ ለንግድ ሥራዋ ግልጽ የሆነ መንገድ አስቀምጦላታል። እንዴት ግን ማሳካት ቻለች?

አንድ ሰው ስኬታማ መሆን ከፈለገና ግልጽ ራዕይ ካለው መቼና የት መድረስ እንደሚፈልግ በግልጽ ማስቀመጥ አለበት።

በሌላ በኩል ከሰዎች ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ነገሮች ስለመኖራቸው ከግምት ውስጥ ማስገባትና የሌሎች ሰዎችንም ሐሳብ ለማካተት ፈቃደኛ መሆን ያስፈልጋል።

ሮዚ ግልጽ የሆነ ዕቅድ ቢኖራትም አንዳንድ ጊዜ ግን ያልታሰቡ ነገሮች ሲያጋጥሙ ማሻሻያዎችን ታደርጋለች። ለዚህም ነው ስኬታማ መሆን ችላም ሠራተኞቿም ደስተኛ መሆን የቻሉት።

ሮዚ እንደምትለው አንድ ሰው ትልቅ ራዕይ ይዞ ሲጀምር ሐሳባቸውን በግልጽ የሚያስቀምጡና በቡድን መሥራት የሚችሉ ጠንካራ ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉት ማሰብ አለበት።

በተጨማሪ ደግሞ ወጣቶች ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግም ታምናለች።

የሮዚ ግልጽ የሆነ ራዕይ ጠንካራ የሆነ የሠራተኞች ግንኙነት እንዲፈጠርና የእሷን ሐሳብ የሚጋሩ በርካታ ወጣቶችን እንድታገኝ ረድቷታል።

ሁሌም ቢሆን የተለያየ አይነት እውቀት እንዲሁም ልምድ ያላቸውን ሰዎች ነው ወደ ድርጅቷ የምታስጠጋው።

ይህ ደግሞ ሁሌም ጠቃሚ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ከጉዳቱ ጥቅሙ ያመዝናል።

ችግሮች በሚፈጠሩ ጊዜም ከሠራተኞቿ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ግልጽ ውይይት ታደርጋለች።

ሰዎች ሐሳባቸው እንደሚሰማና ለድርጅቱ የሆነ ነገር ማበርከት እንደሚችሉ ሲያምኑ የሥራ ተነሳሽነታቸው ይጨምራል ትላለች ሮዚ።

ምንም እንኳን አንዳንዴ ሠራተኞቿ የሚያነሱት ሐሳብ ከእሷ ሐሳብ ጋር በጭራሽ የማይገናኝ ቢሆን እንኳን በተገቢው መንገድ ለማስረዳትና ነገሮችን ለማስተካከል ትሞክራለች።

ባለራዕዮች በርካቶችን ለተሻለ ነገር የማነሳሳታቸው ነገር የሚያጠራጥር ባይሆንም እንዴት አድርገው ከሰዎች ጋር ይነጋገራሉ የሚለው ግን ትልቅ ጥያቄ ነው።

የሰዎችን ሐሳብ መስማትና ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ራዕዩን ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም መዘንጋት የለበትም።