የፖሊስ አባሏ በራሳቸው ተነሳሽነት 6 ሄክታር መሬት በደን ሸፈኑ

በኮማንደር ተናኜ የለማ ደን
የምስሉ መግለጫ, በኮማንደር ተናኜ የለማ ደን

የፖሊስ አባል የሆኑት ኮማንደር ተናኜ ወልዱ በራስ ተነሳሽነት በኢሉአባ ቦራ ዞን የሚገኝ 6 ሄክታር መሬት በደን ሸፈኑ።

ኮማንድር ተናኜ ከልጅነታቸው ጀምሮ ለደን እና አትክልቶች ልዩ ፍቅር እንዳላቸው ይናገራሉ። ኮማንደር ተናኜ አካባቢን በተፈጥሯዊ ደን የመሸፈን ፍላጎት ቢኖራቸውም በገንዘብ እና ቦታ እጦት ምክንያት ፍላጎታቸውን ማሳካት ሳይችሉ መቆየታቸውን ያስረዳሉ።

"ችግኝ መትከል ውስጤን በጣም ያስደስተዋል። ግን ችግኝ የምተክልበት መሬት የለኝም። ገንዘብም የለኝም። በዚህም ምክንያት ሁሉንም ሊጠቅም የሚችል ነገር መስራት የምችልበትን አጋጣሚ መፍጠር አልቻልኩም ነበር" ይላሉ።

ይኹን እንጂ 2003 ዓ.ም. ላይ የኢሉአባ ቦራ ዞን ማረሚያ ቤት አስተዳዳሪ ሆነው ሲሾሙ የልጅነት ፍላጎታቸውን የሚያሳካ አጋጣሚ ማግኘታቸውን ይናገራሉ።

"2003 ላይ የዞኑ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ሆኜ ስመጣ ያሰብኩትን ማሳካት የሚያስችልኝ የረዥም ጊዜ እቅድ አዘጋጀሁ። ከዛ በኋላ አብረውኝ ካሉ ሰዎች ጋር ይህን እቅዴን መተግበር ጀምርኩ" ይላሉ።

ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ባዶ በነበረ መሬት ላይ ችግኝ መትከል መጀመራቸውንም ያስረዳሉ።

"በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ዓይነት ችግኞችን እንተክላለን። ይህን ሥራ ከጀመርኩ ወደ 11 ዓመት ይሆነኛል። እስካሁን ምንም ያልነበረበትን 6 ሄክታር መሬት በደን እንዲሸፈን ማድረግ ችያለሁ" ይላሉ ኮማንደሯ።

አሁን በደን የተሸፈነው መሬት ከዚህ ቀደም ምንም ሊያበቅል አይችልም ተብሎ ባዶውን የተተወ መሬት እንደነበረም ይናገራሉ።

ኮማንደር ተናኜ ከግዙፍ ተክሎች በተጨማሪ ለምግብነት የሚውሉ አትክልት እና ፍራፍሬ በመተከላቸው ምርት መሰብሰብ መቻላቸውንም ያስረዳሉ።

"እንደ አናናስ፣ ሙዝ፣ ጥቅል ጎመን እና ቀይ ስር ያሉ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን እናመርታለን። በተለይ ብዙ ሙዝ በመትከላችን በመቱ ከተማ ለገበያ እያቀረብን ነው።"

ኮማንደር ተናኜ በአሁኑ ሰዓት የኢሉአባ ቦራ ዞን ማረሚያ ቤት አስተዳዳሪ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ። የደን ማልማት ሥራቸውን የሚሰሩት በሚኖራቸው ትርፍ ሰዓት ነው።

ከጥቂት ዓመታት በፊት የኮማንደር ተናኜ የሥራ ውጤት በመንግሥት ኃላፊዎች ተጎብኝቶ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Commander Tenagne Woldu

የምስሉ መግለጫ, ከጥቂት ዓመታት በፊት የኮማንደር ተናኜ የሥራ ውጤት በመንግሥት ኃላፊዎች ተጎብኝቶ ነበር

ኮማንድር ተናኜ የችግኝ ተከላ ሥራቸውን የጀመሩት በማረሚያ ቤቱ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ነበር።

በዚህ የደን ማልማት ሥራ ላይ ፈቃደኛ የሆኑ የማረሚያ ቤቱ ታራሚዎች ጭምር ተሳታፊ እንደሆኑ ኮማንድር ተናኜ ይናገራሉ።

"ደን በማውደም የታሰሩ ብዙ ሰዎች አሉ። እነዚህን የምናርማቸው ችግኝ እንዲተክሉ በማድረግ ነው።" ይላሉ ኮማንደሯ።

6 ሄክታ መሬት በደን ከመሸን ስራቸው በተጨማሪ፤ በመቱ ከተማ 11 ሄክታር መሬት ላይ ለነዋሪዎች መናፈሻ ሊሆን የሚችል ቦታ በደን ለመሸፈን እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

"በዚህ መናፈሻ ቦታ 3 ሄክታር የሚሸፍን ሰው ሰራሽ ሃይቅ አዘጋጅተናል። በዚህ ሰው ሰራሽ ሃይቅ ውስጥ አሳ አርብተን ለገበያ ዝግጁ አድርገናል። በሃይቁ ላይ የጀልባ ጉዞም ጀምረናል። መናፈሻው የልጆች መጫወቻ ቦታም አለው" በማለት ያስረዳሉ።

ኮማንደር ተናኜ አሁን የጡረታ እድሜያቸው እንደተቃረበ ይናገራሉ። ኮማንደሯ በእድሜ እስካለሁ ድረስ የደን ማልማት እና የመንከባከብ ሥራዬ እቀጥላለሁ ይላሉ።