ሳራ ከበደ፡ በአሜሪካ ሚኒሶታ በቀን ከ8ሺህ እንጀራ በላይ እንደምታከፋፍል የምትናገረው ኢትዮጵያዊት

የፎቶው ባለመብት, Sara Kebede
አገሩን ጥሎ ከወጣ ኢትዮጵያዊ ማጀት የማይጠፋው ነገር እንጀራ ነው።
ትኩስ ሽሮ ያራሰው እንጀራ ባይገኝ እንኳ፤ ትኩስ እንጀራ በሚጥሚጣ መጉረስ የማይናፍቅ ኢትዮጵያዊ ማግኘት ዘበት ነው።
ታዲያ አገሩን በልቡ ተሸክሞ ለወጣ ኢትዮጵያዊ፣ አምሮት ቆራጭ ድልድይ ሆነው የሚያገለግሉ እናቶች አይጠፉም።
ጤፉን እንደ አመሉ ከአገሩ ውሃ ጋር አስማምተው፣ እንጀራ የሚጋግሩ ባለሙያዎች ከአፍሪካ እስከ እስያ፣ ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ ከትመዋል።
ሳራ ከበደም በአሜሪካ ሚኒሶታ እንጀራን አሳምራ ትጋግራለች።
ታዲያ ይህ ምኑ ይደንቃል? ለሚል ጠያቂ፣ 'የሚኒሶታ ከተማ ኢትዮጵያዊንን የማያቋርጥ የእንጀራ ፍላጎት ለማሟላት የፈጠረችው ምጣድ' የሚል መልስ አለን።
ሳራ ከበደ እንጀራ ጋግራ በመሸጥ እንጀራ የወጣላት ሴት ናት።
እንጀራ መጋገርን እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የተማረችው ከእናቷ ነው። እጆቿ ለሥራ ሳይደርሱ በፊት ከእናቷ የተማረችው ይህ ሙያ ባሕር ማዶ ተሻግሮ ሕይወቷን በዚህ መልክ ይጽፋል ብላ አስባ አታውቅም።
ግን አሁን በሚኒሶታ በቀን ስምንት ሺህ እንጀራ ጋግራ ታከፋፍላለች።
ይህንን ሁሉ እንጀራ ለመጋገር ለሰዓታት መቆም ቢደክማት ደግሞ እንጀራ የሚጋግር ማሽን ንድፍ አውጥታ ሰርታለች።
አሁን ይህ ማሽን በሰዓት 350 እንጀራ ይጋግራል።
የእርሷን ድካም ሲያቀል፣ የደንበኞቿንም ፍላጎት በሚገባ አሟልቷል።
ሳራ ከበደ ከ20 ዓመት በላይ በአሜሪካ ሚኒሶታ ግዛት የኖረች ሲሆን፣ ቢያንስ በቀን ከስምንት ሺህ በላይ እንጀራ ለደንበኞቿ ታከፋፍላለች።
በአርሲ ሌሙ ቢልቢሎ ተወልዳ ያደገችው ሳራ ወደ አሜሪካ ከማቅናቷ በፊት በስደት ኬንያ ውስጥ ለስምንት ዓመታት ኖራለች።
በኬንያ ካኩማ የስደተኞች መጠለያ አራት ዓመት፣ ከዚያ ቀሪውን አራት ዓመት ደግሞ በናይሮቢ ከተማ ስትኖር ገቢ ማግኛ ሆኖ ኑሮዋን የደጎመው ይኸው የእንጀራ ንግድ ነው።
አሜሪካ የሄደችው በ1992 ዓ.ም ቢሆንም እንጀራን በመጋገር መሸጥ የጀመረችው ግን ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ነው።
ሳራ የእንጀራ ገበያዋ ሲደራ በቀን ከ16 ሰዓት በላይ ቆማ ስትጋግር ትውል እንደነበር ታስታውሳለች፤ ነገር ግን የደንበኞቿን ፍላጎት ማሟላት ፈታኝ ሆኖባት ቆይቷል።
ከዚህ በመነሳትም ለምን በሰዓት ውስጥ ብዙ እንጀራ መጋገር የሚችል ማሽን አልፈጥርም በማለት ሙከራ እንደጀመረች ለቢቢሲ ተናግራለች።
"እኔ ወደ አሜሪካ ከመጣሁ በኋላ እንጀራ እየጋገርኩ ነው የምኖረው። በቀን ከ16 ሰዓት በላይ ቆሜ ስለምጋግር በጣም ያደክመኛል። እንደዚያም ሆኖ ለደንበኞቼ ላዳርስ አልቻልኩም" ትላለች።
ሳራ ይህንን ሃሳቧን ወደ ተግባር ለመለወጥ አምስት ዓመት ያህል ወስዶባታል።

የፎቶው ባለመብት, Sara Kebede
ይህ ማሽን ተግባራዊ ሲሆን ደግሞ በሰዓት 350 እንጀራ በመጋገር እርሷን ከድካም፤ ደንበኞቿንም ከእንጀራ እጦት ታድጓል።
ሳራ እንደምትለው ማሽኑ ራሱ ሊጡን መጥኖ በመቅዳት ያሰፋል።
አስፍቶ ሲጨርስ ደግሞ እንዳይነፍስበት አክንባሎውን በሚገባ ከድኖ በተመጠነለት ሰዓት ይከፍታል።
በዚህም የተነሳ ከዚህ ቀደም ከአንድ በላይ ሰው ይጠይቅ የነበረውን ሥራ አሁን አንድ ሰው ብቻ የሚሰራው ሆኗል።
የዚህ ሰው የሥራ ድርሻም እንጀራውን ከማሽኑ ላይ አውጥቶ ሌማቱ ላይ ማስቀመጥ ብቻ ነው።
ሳራ ይህ ማሽን በራሱ ጊዜ የጋገረውን እንጀራ ራሱ እንዲያወጣ ሞክራ እንደነበር ትናገራለች፤ ነገር ግን በዚያ መሰረት ማሽኑን ለመስራት ውድ በመሆኑ መቅረቱን ትናገራለች።
ይህ ማሽን ከኮምፒውተር ጋር ግንኙነት ስላለው የሙቀቱን መጠን መቆጣጠር እና መከታተል ይቻላል።
ማሽኑ በኤሌትሪክ እና በጋዝ የሚሰራ ሲሆን ለሥራ ጥራትና ወጪ ቁጠባ ሲባል ግን ጋዝ እንደምትጠቀም ገልጻለች።
"ድካም ወደ ፈጠራ መራኝ"
ከልጅነቴ ጀምሮ እንጀራ እየጋገርኩ ነው የኖርኩት። እናም ሥራው ከባድ እና አድካሚ እንደሆነ አውቀዋለሁ ትላለች ሳራ።
"ከዚህ ቀደም ደንበኞቼን ማስከፋት ስለማልፈልግ በድካም ውስጥ ሆኜም እየጋገርኩ ላደርስላቸው እሞክር ነበር" የምትለው ሳራ እንደዚያም ሆኖም ግን ማብቃቃት እንዳልቻለች ትናገራለች።
በምትኖርበት ሚኒሶታ ያለውን የእንጀራ ፍላጎት ለማርካት ሰው ቀጥሮ ለማሰራት ብታስብም እንደ እርሷ እንጀራውን አሳምሮ የሚጋግር ባለሙያ ማግኘት ከብዷት ነበር።
ስለዚህ የኢትዮጵያን እንጀራ ከእናት ጓዳ ባልተናነሰ ጋግሮ የልብ የሚያደርስ ማሽን ለመስራት ንድፍ አወጣች።
ንድፉን ግን ወደ ተጨባጭ ማሽን ቀይሮ የሚያስረክባት ባለሙያ ማግኘት ፈተና ሆነባት።
የመጀመሪያው ፈተና የምታገናቸው ባለሙያዎች ስለእንጀራ ትንሽም ቢሆን እውቀቱ ስላልነበራቸው የምትላቸውን ወደ ተግባር ለመቀየር ፈተና ገጥሟቸው ነበር።
በመጨረሻ ግን የእርሷን የአዕምሮ ውጤት እውን የሚያደርግ ባለሙያ ተገኘ። ይህንን ማሽንም ለአንድ ዓመት ያህል ከሞከረችው በኋላ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ አስገብታዋለች።
ይህን ግን ወደ ተግባር ለመቀየር ዳጎስ ያለ ገንዘብ ጠይቋታል። ለዚያም ነው አምስት ዓመት ያህል የፈጀባት።
ይህንን ማሽን ሰርቶ ለማጠናቀቅ 220 ሺህ ዶላር እንዳወጣች ሳራ ለቢቢሲ ተናግራለች።
አሁን ሳራ በሚኒሶታ ውስጥ ስሟ የገነነ እንጀራ አቅራቢ መሆኗን ትናገራለች። በተጨማሪም የራሷ ግሮሰሪ ስላላት እዚያም ምግብ ትሸጣለች።
"ማሽኑ ከተሰራ በኋላ እኔም ተሳክቶልኛል፤ ምርታችን በደንብ ጨምሯል፤ እኔም ትልቅ እፎይታ አግኝቻለሁ። ማሽኑ አገር ቤት ቢገባ ደግሞ ንግድ ቤት ላላቸው ሰዎች በጣም አትራፊ ይሆናል" ትላለች ሳራ።
በአሜሪካም እንጀራን ጋግረው በማከፋፈል ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ማሽኑን ለመግዛት እንደጠየቋትም ገልጻለች።
















