ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በምሥራቅ ወለጋ በተፈጸመ ጥቃት ሰዎች ተገደሉ ፤ ቤቶች ተቃጠሉ
በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ ነጌሶ እና ሐሮ አያና ተብለው በሚጠሩ ቀበሌዎች ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ሰዎች መገደላቸውን እና መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን ነዋሪዎች እና የአካባቢው ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ተናገሩ።
የጊዳ አያና ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አዳነ አላምረው በነጌሶ እና ሐሮ አያና ቀበሌዎች በተሰነዘረው ጥቃት ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውን እና በርካታ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን ገለጸዋል።
ጨምረውም በአካባቢው ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ወደ ስፍራው ሄደው የደረሰውን የጉዳት መጠን በትክክል ማወቅ እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአከባቢው ነዋሪዎች ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ ደርሷል በተባለው በዚህ ጥቃት ከስምንት ያላነሱ ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል።
የጊዳ አያና ወረዳ ኮሚኒኬሽን በፌስቡክ ገጹ ላይ የካቲት 09/2014 ዓ.ም. ለደረሰው ጥቃት 'በብሔር አማራ' የሆኑ ታጣቂዎችን ተጠያቂ አድርጓል።
የወረዳው የአስተዳዳር እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊው አቶ መስጋና ሞርካ፤ አካባቢው ቀድሞውኑ "የጠላት ቀጠና" ነው ካሉ በኋላ፤ በአካባቢው "ኦነግ ሸኔ እና ጽንፈኛ የአማራ ታጣቂዎች" ይንቀሳቀሳሉ ብለዋል።
"ወደ ቦታው ሄደን የተፈጠረውን ማጣራት አልቻልንም። ያለን መረጃ ግን ጽንፈኛ የአማራ ታጣቂዎች ናቸው ተኩስ ከፍተው ጉዳት ያደረሱት የሚል ነው" በማለት አቶ መስጋና ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ባለሥልጣኑ ጽንፈኛ ያሏቸው የአማራ ታጣቂዎች ማን እንደሆኑና ከየት እንደመጡ የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በምዕራብ ኦሮሚያ፤ በቅርቡ ደግሞ በምዕራብ ሸዋ ዞኖች ብሔር ተኮር ግድያዎች፣ የንብረት ውድመት እና ማፈናቀሎች ተደጋጋሚ ክስተቶች ሆነው ቆይተዋል።
የአማራ ብሔር ተወላጆችን ዒላማ ለሚያደርጉ ጥቃቶች መንግሥት እና ተጎጂዎች እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራውን ታጣቂ ቡድንን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
በኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ ለሚደርሰው ግድያ እና ንብረት ውድመት ደግሞ የአማራ ታጣቂዎች ናቸው ያሏቸውን ተጠያቂ ይደረጋሉ።
እንደማሳያም በቅርቡ በምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ውስጥ በምትገኝ ጫንዶ ቀበሌ መንግሥት ሸኔ እያለ የሚጠረው ቡድን ባደረሰው ጥቃት ከ20 የአማራ ተወላጆች መገደላቸውን የሟች የቤተሰብ አባላት ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ይህ ጥቃት ከደረሰ ከአንድ ወር ገደማ በኋላ ማለትም ጥር 23/2014፤ የአማራ ታጣቂዎች የወሰዱት የበቀል እርምጃ ነው በተባለ ጥቃት 13 የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች መገደላቸውን እና ከ97 በላይ ቤቶች መቃጠላቸውን ነዋሪዎች እና የአካባቢው ባለስልጣናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የጊዳ አያና ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አዳነ አላምረው እንደሚሉት ከሆነ፤ በወረዳው 'ከሸኔ' እና 'ከአማራ ታጣቂዎች' በተጨማሪ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተሻግሮ የሚመጣ ታጣቂ ኃይችል ችግር እየፈጠረ ነው።
በአካባቢው ባለው የፀጥታ ችግርም ጥቃት ወደሚያጋጥምባቸው ስፍራዎች የአካባቢው ባለሥልጣናት መሄድ እንደማይችሉ አቶ አዳነ ጨምረው ተናግረዋል።
ታጣቂዎች ጥቃት በሚሰነዝሩባቸው አካባቢው የመንግሥት መዋቅር እንደሌለ የሚናገሩት የወረዳው አስተዳዳሪ፤ አካባቢዎቹን "ኦነግ-ሸኔ ነው ይዞ የሚገኘው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በወረዳዋ የኦሮሞ እና የአማራ ብሔር ተወላጆች ለበርካታ ዓመታት በሰላም ሲኖሩ መቆየታቸውን ገልጸው፤ በተለያዩ ጊዜያት ወደ ወረዳዋ ሰርገው የገቡ የአማራ እና የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት አድርሰዋል ይላሉ።
"ሁለቱም አካላት ለእኛ ጠላት ናቸው። ለሕዝም ለመንግሥትም ጠላት ናቸው" ይላሉ የጊዳ አያና ወረዳ አስተዳዳሪ።
የጊዳ አያና ወረዳ የአስተዳዳር እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊው አቶ መስጋና ሞርካ ታጣቂዎቹን ለመቆጣጠር በቂ የመንግሥት የፀጥታ ኃይል በስፍራው እንደሌለ አመልክተዋል።
ከዚህ ቀደም ለሕዝብ ፀጥታ ችግር ሆነው የቆዩት "የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ነበሩ አሁን ደግሞ ጽንፈኛ የአማራ ታጣቂዎች ተጨምረውበታል" በማለት አቶ ምስጋና ይናገራሉ።
ከዚህ ቀደም የኦሮሚያ ክልል የአስተዳዳር እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፈ አቶ ሻፊ ሁሴን በምዕራብ ኦሮሚያ የታጣቂዎችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በቂ የመንግሥት የፀጥታ ኃይል መሰማራቱን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
አቶ ሻፊ በወቅቱ፤ "ያለን ኃይል ያለው እዚያ ነው። የአገር መከላከያ፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል፣ መደበኛ ፖሊስ እና ሚሊሻ አለን" በማለት ተናግረው ነበር።