የእስራኤሉ የስለላ ተቋም ሞሳድ የኢራንን ጥብቅ የደኅንነት መዋቅር እንዴት ዘልቆ ገባ?

እአአ በጥቅምት 2020 ታዋቂው ኢራናዊ የኒውክሌር ሳይንቲስት ሞህሴን ፋክኽሪዛደህ ይጓዝበት የነበረው መኪና ጋየ።

በሰው ሠራሽ ክህሎት [አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ] አማካይነት በርቀት ቁጥጥር ከሚደረግበት መትረየስ በተተኮሰ ጥይትም ተገደለ።

ጉዞ ላይ ባለ መኪና ውስጥ የተሳፈረን ኢላማ ከሌሎች ሰዎች ለይቶ በዚህ መንገድ መግደል እጅግ ጠንካራ የስለላ ክህሎትን ይጠይቃል።

ሳይንቲስቱ ከተገደለ በኋላ የኢራን የደኅንነት ኃላፊ ማሕሙድ አልቪ ይህን መሰል ጥቃት ሊሰነዘር እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ሰጥተው እንደነበር ተናግረዋል።

ግድያው ከመፈጸሙ ከሁለት ወራት በፊት፤ ሳይንቲስቱ በተገደለበት ስፍራ አንዳች ጥቃት እንደሚደርስ መሐሙድ አስጠንቅቀው ነበር።

የደኅንነት ኃላፊው እንዳሉት ግድያው የተፈጸመው "በአገሪቱ ጦር ሠራዊት አባል ሲሆን፣ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ደግሞ በወታደራዊ ኃይል ውስጥ ለመንቀሳቀስና እርምጃ ለመውሰድ አይችልም።"

ኃላፊው በቀጥታ ባይናገሩም በተዘዋዋሪ ተጠያቂ ያደረጉት በኢራን እስላማዊ የአብዮታዊ ዘብ ጓድ (ኢስላሚክ ሪቮሉሽን ጋርድ ኮርፕስ) ውስጥ ያለ ሰርጎ ገብን ነው።

ይህ ቡድን በኢራን እጅግ የተከበረ ወታደራዊ ስብስብ ነው።

የደኅንነት ኃላፊው እንደሚሉት ለሳይንቲስቱ ግድያ ተጠያቂው የዚህ ቡድን አባል የሆነ ግለሰብ ከሆነ ያ ሰው የቡድኑ ከፍተኛ አመራር ደረጃ ሳይደርስ አይቀርም።

ይህ ሰው ከደኅንነት ኃላፊው የተሰጠውን ጥቆማ ችላ ብሎ ጥቃቱ በታቀደው ቀን፣ ቦታ እና ሰዓት እንዲከናወን መንገድ ጠርጓል።

ሟቹ ሳይንቲስት የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጓድ አባል እንደነበር ይነገራል።

በእርግጥ የኢራን መንግሥት የቡድኑን አባላት ዝርዝር ለሕዝብ ይፋ አያደርግም።

በቴህራን በሚገኘው ኤርቪን እስር ቤት የሚገኝ የቢቢሲ ምንጭ እንደጠቆመው፤ ለውጭ አገራት በመሰለል የተጠረጠሩ የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች በእስር ቤቱ ታግተዋል።

በዚህ ቡድን የውጭ አገራት ቅርንጫፍ ውስጥ ይሠሩ የነበሩ የቀድሞ የደኅንነት ባለሙያ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ በውጭ አገራት ባሉ በበርካታ የኢራን አምባሳደሮች እንዲሁም የቡድኑ አባላት ላይ መረጃ ሰብስበዋል።

ይህ መረጃ እነዚህ ግለሰቦች ከሴቶች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይጨምራል። ከሴቶች ጋር ስላላቸው ግንኙነት የሚሰበሰበው መረጃ ኋላ ላይ ኢራናውያኑ ከውጭ አገራት ሰላዮች ጋር እንዲተባበሩ ጫና መፍጠሪያ ይሆናል።

እአአ በ2018 ከቴህራን በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ የኢንዱስትሪ ቀጠና ውስጥ ያለ መጋዘን በበርካታ ሰዎች በድንገት ተወረረ።

መጋዘኑን ጥሰው የገቡት ሰዎች ውድ እቃ የተቀመጠባቸውን ሳጥኖች መርጠው ቁልፋቸውን አቀለጡ። ከሰባት ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በመጋዘኑ ውስጥ ከነበሩት 32 ሳጥኖች የ27ቱን ቁልፍ ሰበሩ።

ከዚያም ከባድ የኒውክሌር ምስጢር የያዙ ሰነዶች መዝብረው ተሰወሩ።

ዘረፋው በኢራን ታሪክ እጅግ አሳፋሪው ቢሆንም የኢራን መንግሥት ስለጉዳዩ ብዙ ከማውራት ተቆጠበ።

ከዘረፋው ከሦስት ወራት በኋላ የተዘረፉት ሰነዶች ከኢራን 2,000 ኪሎ ሜትር ርቀው ቴል አቪቭ፣ እስራኤል ተገኙ።

የያኔው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የተዘረፉትን ሰነዶች አስጎበኙ። ሰነዶቹ የሞሳድ ኦፕሬሽን ውጤት እንደሆኑም በይፋ ተናገሩ።

የኢራን ባለሥልጣናት ግን እነዚህ ሰነዶች ሐሰተኛ እንደሆኑና የኢራን መጋዘን እንዳልተዘረፈ አስተባበሉ።

ነሐሴ 2021 ላይ የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሮሀኒ በመጨረሻው የሥልጣን ቀናቸው እስራኤል የኢራንን የኒውክሌር ሰነዶች ዘርፋ ለቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዳሳየች አመኑ።

ኔታንያሁ በ2018 የተሰረቁትን የኢራን ሰነዶች ሲያስጎበኙ የኒውክሌር ሳይንቲስቱ ሞህሴን ፋክኽሪዛደህ በኢራን ምስጢራዊ ኒውክሌር ማብላያ ከሚያስገነቡት ዋነኛው መሆናቸውን ተናግረዋል።

"ዶ/ር ሞህሴን ፋክኽሪዛደህ የሚለውን ስም እንዳትዘነጉ" ሲሉም ኔታንያሁ ተደምጠዋል።

ይህን ካሉ ከሁለት ዓመታት በኋላ ሳይንቲስቱ ተገደለ።

"አታውሩ፣ ተኩሱ"

ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ብዙ የኢራን ታዋቂ የኒውክሌር ሳይንቲስቶች ተገድለዋል።

የኢራን ኒውክሌር ማብላያ ፋብሪካዎች ሥራቸውን የሚያስተጓጉል ስውር ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል።

ኢራን እስካሁን ድረስ ጥቃት አድራሾችን ወይም አቀነባባሪዎችን መያዝ አልቻለችም። የፀጥታ ኃይሏ ጥቃቶቹን ማስቆምም ተስኖታል።

በማሕሙድ አሕመዲንጃድ የመጨረሻው የፕሬዝዳንትነት ዘመን (2013 ገደማ) የኢስላማዊ አብዮት ጠባቂ ቡድን ኮማንደሮች፣ ሃይማኖታዊ አባቶች እንዲሁም የደኅንነት አመራሮች ለሞሳድ በመሰለል ተጠርጥረው ታስረው ነበር።

ስለእስሩ በይፋ የተባለ ነገር ግን የለም።

ተጠርጣሪ ከተባሉት አንዱ በኢራን የእስራኤል ስለላ ቡድን አመራር ነበሩ። በሚስጥር ተከሰው፣ የሞት ፍርድ ተወስኖባቸው፣ በአደባባይ ተገድለዋል።

ማሕሙድ ባለፈው ዓመት "ሞሳድ የደኅንነት ሚኒስቴራችንን ጥሶ መግባቱ እሙን" ሲሉ ተናግረዋል።

አያይዘውም "የእስራኤል ሰላዮችን እንዲቆጣጠር የተመደበው እና የእስራኤል ሰላዮችን ያጋልጣል የተባለው ሰው የእስራኤል ሰላይ ሆኖ ተገኝቷል" ብለዋል።

እስራኤል ስለ ሞሳድ እንቅስቃሴ እምብዛም በይፋ ምላሽ አትሰጥም።

ከእስራኤል መከላከያ ጡረታ የወጡት የቀድሞው አመራር አሞስ ጊላድ እስራኤል ስለ ሞሳድ መረጃ የማትሰጠው ምክንያት ስላላት ነው ይላሉ።

"መረጃን ይፋ ማድረግን እቃወማለሁ። መተኮስ ካስፈለገ ዝም ብሎ መተኮስ ነው። አታውሩ፣ ተኩሱ!" ብለዋል አሞስ።

ጨምረውም "ሞሳድ የሚታወቀው ብዙ በማይወራላቸው ድንቅ ኦፕሬሽኖቹ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የቀድሞው የኢራን አመራሮች ሞሳድ በኢራን የፀጥታ እና የደኅንነት ክፍል እስከ ከፍተኛ አመራሮች የሚደርስ መዋቅር ዘርግቷል ብለው ይሰጋሉ።

የቀድሞው የኢራን የደኅንነት ሚኒስትር እና የሮሐኒ አማካሪ አሊ ዩኒሲ ከዚህ ቀደም ባለደጉት ቃለ ምልልስ "ሞሳድ በኢራን ውስጥ ያለው መዋቅር እስከ ከፍተኛ አመራሮች ስለሚደርስ እያንዳንዱ የኢራን ባለሥልጣን ለሕይወቱ እና ለደኅንነቱ መፍራት አለበት" በማለት ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።