የሶማሊያ መንግሥት መሠረቱን በኢትዮጵያ ያደረገውን ኦብነግ ከአሸባሪዎች ዝርዝር አስወጣ

በሥልጣን ላይ ያለው የሶማሊያ ካቢኔ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሰውን የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባርን (ኦብነግ) ከአሸባሪዎች ዝርዝር ውስጥ ማስወጣቱን አስታወቀ።
የቀድሞው የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስር ሐሰን አሊ ፈይሬ ካቢኔ፣ እአአ በ2017 ኦብነግን አሸባሪ ብሎ ከሰየማቸው ቡድኖች ዝርዝር ውስጥ ያስገባበትን ውሳኔ አስተላልፎ ነበር።
የአሁኑ ካቢኔ ግን ለአራት ዓመታት የቆየውን የሶማሊያ መንግሥትን ውሳኔ ሽሮ ኦብነግን ከአሸባሪዎች ዝርዝር ውስጥ ማስወጣቱን እሑድ ዕለት ይፋ አድርጓል።
በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ውስጥ የትጥቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ኦብነግ በቀድሞው የኢትዮጵያ አስተዳደር በሽብርተኝነት ከተሰየሙ ሦስት ቡድኖች አንዱ ነበረ።
ነገር ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ለውጥ ተካሂዶ ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ አሕመድ ከሦስት ዓመታት በፊት ወደ ሥልጣን ሲመጡ ኦብነግን፣ ኦነግንና ግንቦት ሰባትን ከአሸባሪዎች ዝርዝር መሰረዛቸው ይታወሳል።
ይህንን ውሳኔ ተከትሎ ፓርቲው የሽምቅ እንቅስቃሴውን አቁሞ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል መሸጋገሩን አስታውቆ፣ አባላቱም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።
ሶማሊያ ኦብነግን 'አሸባሪ'ስትል የፈረጀችው ለምን ነበር?
እአአ በ2017 የቀድሞው የሶማሊያ ካቢኔ ኦብነግን አሸባሪ ብሎ ሲፈርጅ ሦስት የውሳኔ ሐሳቦችን አጽድቆ ነበር።
የመጀመሪያው "ኦብነግ አሸባሪ ቡድን ነው" የሚል ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሶማሊያ ኦብነግን በጦር መሣሪያም ይሁን በሌላም መንገድ እንደማትደግፍ መገለጹ ነው።
በሦስተኛ ደረጃ ኦብነግ ሶማሊያ ውስጥ ወታደራዊ ልምምድ የሚያደርግበት፣ የጦር መሣሪያ የሚያከማችበት፣ ወታደር የሚመለምልበት እንዲሁም ለሌሎችም ተግባራት የሚጠቀምበት ካምፕ እንዳይኖረው ተወስኖ ነበር።
ኦብነግ በቀድሞው የሶማሊያ ካቢኔ 'አሸባሪ' ከመባሉ በፊት ሞቃዲሾን ጨምሮ በሌሎችም የሶማሊያ ትልልቅ ከተሞች ነጻ እንቅስቃሴ ያደርግ እንደነበር ይነገራል።
በወቅቱ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መንግሥታት መካከል የተፈጠረውን ግንኙት ተመርኩዞ ሶማሊያ ኦብነግን 'አክራሪ ኃይል' ብላ እንድትፈርጅ የኢትዮጵያ መንግሥት ጫና አሳድሮ እንደነበር ይገለጻል።
ይህንን ጫና ተከትሎም ሶማሊያ ኦብነግን አሸባሪ ዝርዝር ውስጥ ከታው ቆይታለች።

የአብዱልከሪም ሼኽሙሴ ጉዳይ
ከኦብነግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እና መስራቾች መካከል አንዱ የሆኑት አብዱልከሪም ሼኽ ሙሴ እአአ 2017 ነሐሴ አካባቢ በሶማሊያዋ ቦሳሶ ውስጥ በሶማሊያ መንግሥት በቁጥጥር ሥር ውለው ለኢትዮጵያ መንግሥት ተላልፈው ተሰጥተው ነበር።
ለሁለት ዓመት ገደማ በተለምዶ ማዕከላዊ የሚባለው እስር ቤት ከቆዩ በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት ጋር በተያያዘ ተለቀዋል።
ሥልጣን ላይ ያለው የሶማሊያ ካቢኔ አብዱልከሪም ተላልፈው መሰጠታቸው "ትክክለኛ ውሳኔ አልነበረም" ማለቱ ተዘግቧል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ኦብነግ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና ግንቦት ሰባትን በአሸባሪ ዝርዝር ውስጥ አስገብቶ በነበረበት ወቅት በጥብቅ ይፈልጋቸው ከነበሩት ግለሰቦች መካከል አንዱ አብዱልከሪም ነበሩ።
አብዱልከሪም ከዚህ ቀደም ከቢቢሲ ሶማልኛ ጋር ባደገሩት ቆይታ "ሕይወቴን በሙሉ በትግል የማሳልፍ ቢሆንም ከዕድሜ መግፋት ጋር በተያያዘ በኦብነግ ውስጥ ያለኝን ሚና ቀንሻለሁ። አሁን መሣሪያ አስቀምጠን በሰላም እየታገልን ነው" ብለዋል።
አብዱልከሪም በአሁኑ ወቅት በኦብነግ አመራርነት ላይ ባይገኙም፤ በፓርቲው ውስጥ ተሰሚነት ካላቸው ግለሰቦች መካከል እንደሆኑ ይነገራል።
ቡድኑ የሽምቅ ትግል በሚያደርግበት ጊዜ በሶማሌ ክልል ውስጥ ኦብነግ ያካሄዳቸውን አብዛኞቹን ኦፕሬሽኖች ከመሩ ከፍተኛ የጦር አመራሮች መካከል አንዱ እንደሆኑም ይጠቀሳል።
ውሳኔው ከሶማሊያ ባለሥልጣናት ሽኩቻ ጋር ይገናኛል?
አምና የፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ምክር ቤት፤ ኦብነግ እአአ በ2017 የሽብርተኞች ዝርዝር ውስጥ እንዲገባ መወሰኑ እንዲሁም የፓርቲው ከፍተኛ ባለሥልጣን አብዱልከሪም ሼኽ ሙሴ ለኢትዮጵያ ተላልፈው እንዲሰጡ መደረጉ ትክክል አልነበም ሲል በድምጽ ብልጫ ወስኖ ነበር።
ይህ የምክር ቤቱ ውሳኔ ግን ተግባራዊ አልተደረገም ነበር።
የሶማሊያን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች እንደሚሉት፤ በፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ እና በጠቅላይ ሚኒስትር ሞሐመድ ሮብሌ መካከል የተፈጠረው መቃቃር አንዳቸው የሌላኛውን ውሳኔ ክፍተት ወደማጋለጥ እያደረሳቸው መጥቷል።
ኦብነግን ከሽብርተኛነት ዝርዝር የማስውጣት ውሳኔ በይፋ የጸደቀው በሞሐመድ ሮብሌ ካቢኔ አማካይነት ነው።
ኦብነግ ከሽብርተኞች ዝርዝር እንዲወጣ መወሰኑም ከወቅታዊው የሶማሊያ ፖለቲካ ግለት ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ተንታኞች መላ ምት ያስቀምጣሉ።
ኦብነግ ስለ ውሳኔው ምን አለ?
የኢትዮጵያ መንግሥት ቡድኑን ከሽብርተኞች ዝርዝር ውስጥ ካስወጣው ዓመታት ቢቆጠሩም፤ በሶማሊያ ውስጥ ግን የኦብነግ ስም በሽብርተኛነት ከተሰየሙ ቡድኖች መካከል ቆይቷል።
የኦብነግ ቃል አቀባይ አብዱልቃድር ሐሰን ሒርሞጌ (ወይም አዳኒ) ፓርቲያቸው በሶማሊያ ካቢኔ ውሳኔ ደስተኛ መሆኑን ለቢቢሲ ሶማልኛ ተናግረዋል።
"ውሳኔው ትክክል አልነበረም። ጠቅላይ ሚኒስትር ሮብሌ የጎደፈውን የሶማሊያ ታሪክና ዝና መልሰዋል" ሲሉ አስተያየታቸው ሰጥተዋል።
ኦብነግ በተደጋጋሚ የሶማሊያ መንግሥት ከሽብርተኛነት ዝርዝር እንዲያስወጣው ቢጠይቅም በጎ ምላሽ እንዳላገኙ ጠቅሰው "በወቅቱ ለእኛ ምላሽ አልሰጡም ነበር። አሁን ግን ባለቀ ሰዓትም ቢሆን ስህተት መሥራታቸውን መቀበላቸውን በበጎ እንመለከተዋለን" ብለዋል።
እአአ በ2017 አሸባሪ ተብለው መፈረጃቸው "በትግላችን ላይ ምንም ተጽዕኖ አላሳደረብንም" ሲሉም ቃል አቀባዩ አክለዋል።
ኦብነግ የትጥቅ ትግል አቁሞ ወደ ኢትዮጵያ አባላቱ ከመመለሳቸው በፊት አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አውስራሊያ፣ ኬንያ እና ኤርትራን ጨምሮ ወደ 60 በሚጠጉ አገራት ቢሮዎች ከፍቶ ይንቀሳቀስ እንደነበር ይነገራል።
የቀድሞው የሶማሊያ ካቢኔ ፓርቲውን አሸባሪ ማለቱ "የሶማሌ ክልል እና የሶማሊያን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ያሻከረ" ውሳኔ ሲሉ ቃል አቀባዩ አብዱልቃድር ገልጸውታል።
"እኛም ህወሓት መራሹን የኢትዮጵያ መንግሥት አሸባሪ ብለነው ስለነበር የያኔው የኢትዮጵያ መንግሥት እኛን አሸባሪ ማለቱ አልገረመንም" ብለዋል።
ኦብነግ ወደ ሰላማዊ ትግል መግባቱን ይፋ ካደረ በኋላ በአገር አቀፍ ምርጫው ለመሳተፍ ተመዝግቦ የነበረ ቢሆንም፤ የመንግሥት ጫናን በምክንያትነት በመጥቀስ ከምርጫው ራሱን አግልሏል።
ቃል አቀባዩ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ "ምንም እንኳን በተለያዩ አገራት ብንሆንም፣ ምንም እንኳን በሶማሌ ላንድ፣ በሞቃዲሾ፣ በኬንያ ብንኖርም የሶማሌ ሕዝብ በዘር፣ በቋንቋ፣ በሃይማት፣ በባህል ተሳስሮ ይቀጥላል። የተወሰኑ ፖለቲከኞች ውሳኔ አይከፋፍለንም" ሲሉም አቋማቸውን አንጸባርቀዋል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ ዑመር በይፋዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ "የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ እናደንቃለን። እንቀበላለን" ብለዋል።
አያይዘውም "ኦብነግ ህወሓት መራሹን መንግሥት በትጥቅ ትግል ተዋግቷል። ለእኛ የነጻነት ታጋዮች ናቸው። አሸባሪ የተባሉበት ውሳኔ ሶማሌ ክልል እና ሶማሊያ ያላቸውን ግንኙነት ያሻከረ ነበር" ሲሉ ጽፈዋል።












