ከአፍሪካ በአውሮፕላን ጎማ ውስጥ ተደብቆ አምስተርዳም የገባው ኬንያዊ መሆኑ ተገለጸ

የአውሮፕላን ጎማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኔዘርላንድስ ፖሊስ እሁድ ከደቡብ አፍሪካ በተነሳ የአውሮፕላን ጎማ ክፍል ውስጥ ተደብቆ በሕይወት አምስተርዳም የደረሰው ግለሰብ የ22 ዓመት ወጣት ኬንያዊ መሆኑን እንዳረጋገጠ ገለጸ።

በአሁኑ ወቅት ነቅቶ ከሰዎች ጋር መነጋገር እንደቻለ የተነገረውና በሕክምና ላይ የሚገኘው ወጣቱ በኔዘርላንድስ ለመቆየት የጥገኝነት ጥያቄ ለማቅረብ እንዳቀደም ተገልጿል።

ወጣቱ ከደቡብ አፍሪካዋ ጆሃንስበርግ ተነስቶ በኬንያ ናይሮቢ በኩል ወደ ኔዘርላንስ ዋና ከተማ አምስተርዳም የተጓዘው ካርጎሉክስ በተባለው የበረራ አገለግሎት የጭነት አውሮፕላን ላይ ተደብቆ ነው።

ፖሊስ ግለሰቡ በአውሮፕላኑ የጎማ ክፍል ውስጥ ተደብቆ የተጓዘው ከደቡብ አፍሪካ ወይስ ከኬንያ የሚለውን ለመለየት ምርመራ እያደረገ ነው።

በአውሮፕላን ጎማ ተንጠላጥለው አገር ለማቋረጥ የሚሞክሩ ሰዎች አውሮፕላኑ የሚበርበት ከፍታ ላይ በቂ ኦክስጅን ስለማያገኙ እና በቅዝቃዜ ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ ጉዞ ላይ ሳሉ ይሞታሉ።

ይህ ግለሰብ ግን በሕይወት ኔዘርላንድ አምስተርዳም አውሮፕላን ማረፊያ ደርሷል። ጉዞው የሚወስደው 11 ሰዓት ገደማ ሲሆን፤ አውሮፕላኑ ኬንያ፣ ናይሮቢ አርፎም ነበር።

የደች ፖሊስ ቃል አቀባይ ጆና ሄልሞንድስ ለኤኤፍፒ እንዳሉት፤ ግለሰቡ የተገኘው የአውሮፕላኑ የፊት ጎማ አካባቢ ነው። ወዲያውም ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

"በሕይወት መገኘቱ እጅግ አስደናቂ ነው" ብለዋል ቃል አቀባይዋ።

የኔዘርላንድ ወታደራዊ ፖሊስ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ግለሰቡ "በአገሪቱ ለመቆየት ጥገኝነት ይጠይቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ አሁን ግን ቅድሚያ የሚሰጠው የጤንነቱ ሁኔታ ነው" ብለዋል።

የደቹ ኤንኦኤስ እንደዘገበው፤ አምቡላንስ በቦታው ሲደርስ የግለሰቡ ሙቀት ከፍ ብሎ ነው የተገኘው። መሠረታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስም አቅም ነበረው።

አውሮፕላኑ ከደቡብ አፍሪካ ከተነሳ በኋላ ወደ መዳረሻው አምስተርዳም ከመድረሱ በፊት ኬንያ መቆሙን ገልጸው፤ ግለሰቡ አውሮፕላኑ ጎማ ላይ የተንጠላጠለው ከደቡብ አፍሪካ ጀምሮ ይሁን ከኬንያ ገና እንዳልታወቀ ገልጸዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ወደ ሰባት የሚደርሱ በአውሮፕላን ውስጥ ተደብቆ ወደ ኔዘርላንድ የመግባት ክስተቶች የነበሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ሁለቱ ብቻ ናቸው በሕይወት ተርፈው የተገኙት።