ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሆዳ ሙታና፡ የአላባማዋ የአይኤስ ሙሽራ ወደ አሜሪካ ለመመለስ ያቀረበችው ይግባኝ ውድቅ ተደረገ
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እስላማዊ ታጣቂ ቡድኑን (አይኤስ)ን የተቀላቀለችው አሜሪካዊት ሴት እንደገና ወደ አገሪቷ ለመግባት ያቀረበችውን ይግባኝ ለመስማት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ።
ሆዳ ሙታና የተባለችው ሴት ያደገችው በአሜሪካ ደቡብ ምሥራቅ ክፍል በምትገኘው አላባማ ግዛት ሲሆን አይኤስን ለመቀላቀል ወደ ሶሪያ ያቀናችው እአአ በ2014 ነበር።
ከአገር ወጥታ በነበረችበት ወቅትም ባለሥልጣናት አሁን የ27 ዓመት ወጣት የሆነችው ሙታና አሜሪካዊ ዜግነት እንደሌላት ወስነው ፓስፖርቷን ሰርዘዋል።
ከዚያም እአአ በ2019 የሙታና አባት ልጃቸው ወደ አገሪቷ እንዳትገባ በከለከለው የፌደራል ፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ ይግባኝ ጠይቀው ነበር።
ይሁን እንጅ ረቡዕ ዕለት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ምንም አስተያየት ሳይሰጥ የጠየቁትን ይግባኝ ውድቅ አድርጎታል።
የየመን ዲፕሎማት ልጅ የሆነችው ሙታና የተወለደችው በአሜሪካ ነው፤ ነገር ግን በፌደራል ሕግ መሠረት አሜሪካ የተወለዱ የዲፕሎማት ልጆች ወዲያውኑ ዜግነት አይሰጣቸውም።
አባቷ አሕመድ አሊ ግን በክሳቸው ላይ ቤተሰባቸው ዲፕሎማሲያዊ ሥልጣን የተሰጣቸው ልጃቸው ከመወለዷ በፊት እንደሆነና ይህም ዜጋ እንደሚያደርጋት አስረድተዋል።
አቶ አህመድ አክለውም ሙታና ከዚህ ቀደም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እንደ ዜጋ እውቅና አግኝታ እአአ በ2004 ፓስፖርት ተሰጥቷታል ብለዋል።
በርካቶች የሙታናን ጉዳይ በዩናይትድ ኪንግደም ከተወለደችውና አይኤስን በመቀላቀሏ የእንግሊዝ ዜግነቷን ከተነጠቀችው ታዳጊ ሻሚማ ቤገም ጋር አነጻጽረውታል።
ሙታና እአአ በ2019 ለሲኤንኤን በሰጠችው መግለጫ አሜሪካን ለቅቃ ወደ ሶሪያ ስትሄድ " ምንም ልምድ የሌላት የዋህ ፣ ቁጡና ትዕቢተኛ ወጣት" እንደነበረች ተናግራለች።
ለጉዞዋ የሚሆናትን ገንዘብ ለማግኘትም ቤተሰቦቿ ሳያውቁ የኮሌጂ ትምህርቷን አቋርጣ ለትምህርት የተሰጣትን ገንዘብ ወደ ቱርክ ለመሄድ ትኬት እንደቆረጠችበት ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ገልጻለች።
ሙታና ከአክራሪ እስላማዊ ቡድኑ ጋር በነበረችበት ወቅትም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሽብር ጥቃቶችን ያደነቀች ሲሆን ሌሎች አሜሪካውያንም አይኤስን እንዲቀላቀሉ አበረታታለች።
በኒው ዮርክ ታይምስ በተገኘውና በትዊተር ገጿ ላይ ባሰፈረችው ጽሁፍ " በጣም ብዙ አውስትራሊያውያን እና እንግሊዛውያን እዚህ ናቸው፤ ግን አሜሪካውያን የት ናቸው? እናንተ ፈሪዎች ተነሱ!" ብላ ነበር።
ሙታና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አይኤስን በቀላቀሏ በጥልቅ እንደተጸጸተች በመግለጽ ቡድኑን በማበረታታት በማኅበራዊ ሚዲያ ላጋራችው ጽሁፍ ይቅርታ ጠይቃለች። ሙታና አሁን ቡድኑ ጋር በነበረችበት ወቅት ከተዋወቀችው ሰው የወለደችው ሕጻን ልጅ አላት።
አባቱ ሞቷል። አሁን እርሷም የት እንዳለችም ግልጽ አይደለም።