በሩዋንዳ ከሙዝ የተጠመቀ መጠጥ የጠጡ 11 ሰዎች ሞቱ

ሙዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሩዋንዳ ደቡብ ምስራቅ ግዛት በምትገኘው ቡጌሴራ ግዛት ከሙዝ የተጠመቀ መጠጥ የጠጡ 11 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።

ከፈረንጆቹ የገና በዓል ጀምሮ ከሙዝ የተጠመቀውን መጠጥ ከጠጡት መካከል 11ዱ ሰዎች መሞታቸውን የሩዋንዳ ወንጀል ምርመራ ቢሮ አረጋግጧል።

ከሟቾቹ በተጨማሪ መጠጡን የጠጡ 4 ሰዎች የጤና መቃወስ አጋጥሟቸው በሆስፒታል ሕክምና እየተከታተሉ ነው ተብሏል።

በሟቾች ላይ በተካሄደ ምርመራ በሆዳቸው ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ሜታሎን የተሰኘ ኬሚካል መገኘቱን የሩዋንዳ ምግብ እና መድሃኒት ባለስልጣን አስታውቋል።

ሜታሎን አልኮል የሰው ልጆች በዕለት ተዕለት ሕይወት የሚጠቀሙባቸው ቁሶችን ለመስራት የሚውል ሲሆን፤ ይህ ኬሚካል በኢንዱስትሪ ደረጃ ይመረታል።

ለሰዎቹ መሞት ምክንያቱም ሜታሎን በከፍተኛ መጠን የሰዎቹ ሰውነት ውስጥ መግባቱ ሳይሆን አይቀርም ተብሏል።

የሩዋንዳ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መጠጡን የጠመቀው ድርጅት ባለቤትን ጨምሮ አምስት ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቋል።

ባለስልጣኑ ጨምሮም መጥመቂያው ሥራውን ሲያከናውን የነበረው ተገቢው ፍቃድ ሳይኖረው ነበር ያለ ሲሆን፤ ድርጅቱ ሥራውን እንዲያቆም ተደርጓል ብሏል።

ለ11 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን ክስተት ተከትሎ በመላው ሩዋንዳ ፍቃድ የሌላቸው መጠጥ መጥመቂያ ስፍራዎች ላይ ክልከላዎችን ለመጣል አገር አቀፍ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።