ትውልደ ኤርትራዊው በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ኬንያ ውስጥ ተይዞ ለኔዘርላንድስ ተላልፎ ተሰጠ

በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ለዓመታት ሲፈለግ የቆየው ትውልደ ኤርትራዊው የኔዘርላንድ ዜጋ ናይሮቢ ውስጥ ተይዞ ለኔዘርላንድስ ተላልፎ መሰጠቱን የኬንያ ፖሊስ አስታወቀ።

ዓለም አቀፍ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ቡድንን ሲያንቀሳቅስ ነበር የተባለው የ53 ዓመቱ ጆን ሐብቴ፣ ከሁለት ሳምንት በፊት ነው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው።

ግለሰቡ ለመያዝ ዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም ኢንተርፖል አስቸኳይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣቱን ተከትሎ፣ የኬንያ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቡድን አባላት በዋና ከተማዋ ናይሮቢ ዳርቻ ላይ በሚገኝ ስፍራ በቁጥጥር ስር እንዳዋሉት ገልፀዋል።

ተጠርጣሪው ናይሮቢ ውስጥ ለምን ያህል ጊዜ ተደብቆ እንደቆየ ባይታወቅም፣ ከሁለት ሳምንት በፊት ነው በቁጥጥር ስር የዋለው። ግለሰቡ ወዲያውኑ ለኔዘርላንድስ ተላልፎ የተሰጠ በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ እዚያው በእስር ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ጆን ሐብቴ በድብቅ የሚንቀሳቀስ ዓለም አቀፍ በሕገወጥ መንገድ ሰዎችን የሚያዘዋውር ቡድን መሪ እንደሆነ እንደሚታመን ኢንተርፖል አመልክቶ፣ በርካታ ሰዎችን ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ በሕገ ወጥ መንገድ በማዘዋወር ወንጀል ተጠያቂ ነውም ተብሏል።

ግለሰቡ በተለይ በርካታ ኤርትራውያንን በእስያ በኩል ወደ አውሮፓ እንዲገቡ አድርገዋል ከተባሉ፣ ቢያንስ አራት የተለያዩ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀሎች ጋር ስሙ ተያይዞ ይነሳል።

የኬንያ ፖሊስ እንዳለው ጆን ሐብቴ ከተያዘ በኋላ የግለሰቡ በግዛቱ ውስጥ መቆየት ከአገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም ጋር የሚቃረን መሆኑን በመግለጽ በአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ፍሬድ ማቲያንጌ ትዕዛዝ ወዲያውኑ ለኔዘርላንድ ተላልፎ ተሰጥቷል።

ጆን ሐብቴ የፍርድ ሂደቱን በኔዘርላንድስ እስር ቤት ሆኖ የሚከታተል ሲሆን፣ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ ስምንት ዓመት የሚደርስ እስር እንደሚጠብቀው ኢንተርፖል ገልጿል።

ትውልደ ኤርትራዊው ጆን ሐብቴ፣ በሚያውቁት ሰዎች ዘንድ 'ኦባማ' የሚል ቅጽል ስም እንዳለው የሚነገር ሲሆን፣ ስደተኞችን ከአፍሪካ የሩቅ ምሥራቅ አገራት በሆኑት በሴንጋፖርና በፊሊፒንስ በኩል በማድረግ ወደ አውሮፓ ያዘዋውር እንደነበር ተገልጿል።

አንዳንዶች በሺዎች የሚቆጠር ዶላር ከፍለው ወደ እነዚህ አገራት ከገቡ በኋላ ገንዘባቸውን ጨርሰው ወደየትም መሄድ ሳይችሉ ቀርተው በሕገ ወጥ መንገድ በመግባት ጥፋት ተይዘው እስር ላይ መሆናቸው ይነገራል።