ስሪ ላንካ ያለባትን የነዳጅ ግዢ እዳ በሻይ ቅጠል ምርት ለኢራን ልትከፍል ነው

የሻይ ቅጠል ሲሰበሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ስሪ ላንካ ከዚህ ቀደም ከኢራን ለገዛችው ነዳጅ ያለባትን እዳ በሻ ቅጠል ምርት ልትከፍል መሆኑን የአገሪቱ ሚኒስትር አስታወቁ።

ስሪ ላንካ የተጠራቀመባትን የ251 ሚሊዮን ዶላር የነዳጅ ዘይት እዳዋን ለመክፈል በየወሩ 5 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የሻይ ቅጠል ምርት ወደ ኢራን ለመላክ አቅዳለች።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከቱሪስቶች ታገኝ የነበረውን ከፍተኛ ገቢዋን ያጣችው ስሪ ላንካ በከፍተኛ ብድርና በውጭ ምንዛሬ እጥረት እየተሰቃየች ትገኛለች።

በሻይ ቅጠል ምርቷ የምትታወቀው ስሪ ላንካ አንድ ባለሥልጣን እንዳሉት አገሪቱ ሻይ ቅጠልን ለሌላ ምርት መለወጫ አድርጋ ስታቀርብ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ባለሥልጣኑ ጨማረውም ይህ ስሪ ላንካ እዳዋን በሻይ ቅጠል ለመክፈል ያቀረበችው ዘዴ በተባበሩት መንግሥታት እና በአሜሪካ አማካይነት በኢራን ላይ የተጣለውን ማዕቀብ የሚጥስ አይደለም ብለዋል።

እንደምክንያትም ሻይ ቅጠል ከሰብአዊ አገልግሎት ሸቀጦች ውስጥ እንደ ምግብ ምርት የሚታይ በመሆኑ እንዲሁም ልውውጡ ጥቁር መዝገብ ውስጥ የገቡ የኢራን ባንኮችን ስለማያካትት መሆኑን አመልክተዋል።

"ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ከኢራን ተገዝቶ ሳይከፈል የቆየውን የነዳጅ ዘይት ዕዳ ለመሸፈን በየወሩ 5 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የሻይ ቅጠል ምርት ለመላክ አስበናል" ሲሉ ባለሥልጣኑ ለሮይተርስ ገልጸዋል።

የሻይ ቅጠል ልማት ሚኒስቴር "ይህ የዕዳ ክፍያ መንገድ የሻይ ቅጠል ምርትን በማቅረብ ስሪ ላንካ በጣሙን የምትፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ያድንላታል" ብሏል።

የስሪ ላንካ የሻይ ቅጠል አምራቾች ማኅበር ቃል አቀባይ ግን ይህ ምርትን በአይነት የመለዋወጡ ዘዴ የሻይ ቅጠል ላኪዎችን ተጠቃሚ የማያደርግና ችግሩን ለመሸፈኛ ብቻ የሚያገለግል ነው ሲሉ ተችተውታል።

ከፍተኛ የውጭ እዳ ያለባት ስሪ ላንካ በአገሯ ውስጥ ያለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት በከፍተኛ ደረጃ በማሽቆልቆሉ ለከባድ ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ መጋለጧ ይነገራል።

በሻይ ቅጠል አምራችነቷ የምትታወቀው ስሪ ላንካ በዓመት 340 ሚሊዮን ኪሎ ግራም የሚመዝን ሻይ ቅጠል ታመርታለች።

ባለፈው ዓመት የፈረንጆች 265.5 ሚሊዮን ኪሎ ግራም ሻይ ቅጠል ወደ ውጭ አገራት ልካ 1.24 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታ ነበር።

ከሕዝቧ 5 በመቶ የሚጠጋው ደግሞ ሻይ ቅጠልን ከተራራማዎቹ የሻይ እርሻዎች በመልቀምና በፋብሪካዎች ውስጥ በማቀነባበር ሥራ ላይ ተሰማርቶ ገቢ ያገኛል።