አሜሪካ ውስጥ የ110 ዓመት እስር የተፈረደበት አሽከርካሪ ጉዳይ ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Lakewood Police Department/Fb
አሜሪካ ኮሎራዶ ግዛት ውስጥ አንድ የከባድ መኪና አሸከርካሪ ከሁለት ዓመት በፊት ፍሬን እምቢ ብሎት በአራት ሰዎች ላይ ለደረሰው የሞት አደጋ ጥፋተኛ ተብሎ የተላለፈበት ፍርድ ቁጣን ቀሰቀሰ።
የ26 ዓመቱ ወጣት ሾፌር ሮጄል አጉሌራ ሜዴሮስ በመኪና አደጋው ምክንያት በቀረቡበት 27 ክሶች ጥፋተኛ ተብሎ የ110 ዓመት እስር የተፈረደበት ሲሆን ዳኛው ይህንን ውሳኔ እንዲያሳልፉ ጫና እንደገጠማቸው ተናግረዋል።
ይህ የፍርድ ውሳኔው ከተሰማ በኋላ አሜሪካ ውስጥ ቁጣ ተቀስቅሶ አሽከርካሪው ምህረት እንዲደረግለት ኪም ካርዳሺያንን ጨምሮ 4.5 ሚሊዮን ሰዎች በፊርማ ጠይቀዋል።
ይህንንም የኮሎራዶ ግዛት ገዢ ጃሬድ ፖሊስ ጽህፈት ቤታቸው ጉዳዩን እየመረመረው መሆኑን የገለጹ ሲሆን የአካባቢው ዐቃቤ ሕግም ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን መልሶ እንዲያጤነው ጠይቋል።
የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ የከባድ መኪና ሾፌሮች ወደ ኮሎራዶ ግዛት ላለመሄድ እንደሚወስኑ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አሳውቀዋል።
የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈበት አጉሌራ ሜዴሮስ አሰቃቂው አደጋ ያጋጠመው ጣውላ ጭኖ ኮሎራዶ ውስጥ በሚገኘው ሮኪ ማውንቴንስ በሚባለው ተራራማ አካባቢ ሲጓዝ ነበር።
የጭነት መኪናው ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ቁልቁል በመሄድ ቆመው የነበሩ መኪኖችን የገጨ ሲሆን በዚህም ሳቢያ እሳት ተነስቶ አደጋውን አስከፊ አድርጎት ለአራት ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል።
ወጣቱ አሽከርካሪ አደጋው የተከሰተው የመኪናው ፍሬን አልሰራ ብሎት እንደሆነና በርካታ መኪኖችን ከመግጨት ለማትረፍ የሚችለውን ሁሉ ማድረጉን ለባለሥልጣናት ተናግሯል።
ሾፌሩ ችሎት ላይ የታደሙትን የሟቾችን ቤተሰቦች እምባውን እያፈሰሰ ይቅርታ እንዲያደርጉለት ጠይቋል።
"ወንጀለኛ አይደለሁም፤ በህይወት ዘመኔ ሁሉ ማንም ሰው ላይ ጉዳት ለማድረስ አስቤ አላውቅም" በማለት አደጋው ከቁጥጥሩ ውጪ በሆነ ሁኔታ መከሰቱን ገልጿል።
ነገር ግን ዐቃቤ ሕግ የ26 ዓመቱ አሽከርካሪ የጭነት መኪናው ፍሬን ላይሰራ እንደሚችል ያውቅ ነበር ሲል የተከራከረ ሲሆን፤ ጨምሮም በአደገኛ ሁኔታ በመኪኖች መካከል እያቆራረጠ ይጓዝ እንደነበረና በመንገድ ላይ ችግር ለገጠማቸው ተሽከርካሪዎች ማቆሚያ የሚያገለግል ቢያንስ አንድ ቦታን አልፎ ሄዷል ብሏል።
ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት ሮጄል አጉሌራ ሜዴሮስ በተሽከርካሪ የሰው ህይወትን ማጥፋትና በተሽከርካሪ ጉዳት ማድረስን ጨምሮ በቀረቡበት ከ20 በላይ ክሶች ጥፋተኛ ብሎታል።
ነገር ግን የተላለፈበት የ110 ዓመት እስር ውዝግብን በመቀስቀስ ውሳኔው እንዲቀለበስ ጥሪ እየቀረበ ይገኛል።
ዳኛ ብሩስ ጆንስ በችሎት ላይ እንደተናገሩት በኮሎራዶ ሕግ መሠረት ተከሳሹ ጥፋተኛ ለሆነባቸው ክሶች ዝቅተኛውን ቅጣት በመበየን አንድ በአንድ ተፈጻሚ መደረግ አለባቸው ብለዋል።
ኩባዊ ዜግነት ያለው ተከሳሹ አሽከርካሪ ከዚህ በፊት ምንም አይነት የወንጀል ክስ የሌለበት ሲሆን ባለሥልጣናትም በአደጋው ወቅት አሽከርካሪው አልኮልም ሆነ እጽ እንዳልተጠቀመ አረጋግጠዋል።
ከውሳኔው በኋላ የተከሳሹ ሮጄል አጉሌራ ሜዴሮስ ጠበቃ ውሳኔው እንዲመረመርላቸው ይግባኝ እንደሚጠይቁ አመልክተዋል።












