ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለሦስት ወራት ለሚጠጋ ጊዜ በእስር የቆዩት አቶ አብረሃ ደስታ ተፈቱ
ላለፉት ሦስት ወራት ገደማ በእስር ላይ የቆዩት የአረና ትግራይ ፓርቲ ሊቀመንበርና የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራር የነበሩት አቶ አብረሃ ደስታ ከእስር ተፈቱ።
የአቶ አብረሃ ወንድም አቶ ተወልደ ደስታ ለቢቢሲ እንደገለጹት ፖለቲከኛው አቶ አብረሃ ከእስር ቤት የወጡት በአስር ሺህ ብር ዋስ ነው።
አቶ አብረሃ ደስታ መፈታታቸውን አስመልክተው በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ "ከ82 ቀናት የእስር ቤት ቆይታ በኋላ በ10 ሺህ ብር ዋስ ተፈትቻለሁ" ብለዋል።
አቶ ተወልደ ወንድማቸው አቶ አብረሃ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ማዕከላዊ እስር ቤት መቆየታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"አሁን ባለውን ወቅታዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ይመስለኛል በ10ሺህ ብር ዋስ የተፈታው። መስከረም 20 ከታሰረ ወዲህ ሦስት ወራት ከሚጠጋ ቆይታ በኋላ ነው ከእስር የወጣው።"
ከወራት በፊት አቶ አብረሃ ደስታ ሰኔ ወር ላይ ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ተከራይተው ይኖርቡት ከነበረ ሆቴል በፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ቤተሰቦቻቸውና የአረና ፓርቲ ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
አቶ አብረሃ አርፈውበት ከነበረው አራት ኪሎ አካባቢ ከሚገኝ ሆቴል በሁለት አጃቢዎችና ሌሎች የሲቪል ልብስ በለበሱ የደኅንነት ሰዎች በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት፣ ሕገ ወጥ መሣሪያ መያዛቸው በፖሊስ እንደተነገራቸው የቤተሰባቸው አባል ለቢቢሲ ገልጠው ነበር።
አቶ አብረሃ ደግሞ መሣሪያው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሰጣቸው መሆኑን ከመግለጻቸውም በላይ ከነሰነዱ ጋር ለፀጥታ አካላት እንደሰጡና ፖሊስም በዚህ ሰነድ ላይ እንደፈረመ በወቅቱ እኚሁ የቤተሰባቸው አባል ተናግረው ነበር።
ፖሊስ አቶ አብረሃ ደስታ በቁጥጥር ሥር ስለዋሉበት ምክንያት በይፋ ያለው ነገር ባይኖርም፣ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአቶ አብረሃ ቤተሰብ ግን ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ይዘዋል በሚል ክስ እንደተመሰረተባቸው በጊዜው ገልጠዋል።
አቶ አብረሃ ደስታ ትግራይ ውስጥ ጦርነቱ በተጀመረ ሰሞን በጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አሕመድ በተቋቋመው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ለስድስት ወራት የሰሩ ሲሆን፣ የመንግሥት ኃይሎች ከትግራይ ሲወጡ ወደ አዲስ አበባ መሄዳቸው ይታወሳል።
አቶ አብረሃ በአዲስ አበባ በትግራይ ተወላጆች ላይ ይደረጋል ባሉት የጅምላ እስር በማኅበራዊ ሚዲያ ተቃውሟቸውን ይገልጹ እንደነበር አይዘነጋም።
አቶ አብረሃ ከ2007 ምርጫ ቀደም ብሎ ሐምሌ 2006 ዓ.ም በቀድሞው ኢህአዴግ አስተዳደር ጊዜ ከግንቦት 7 እና ከደምሂት ፓርቲ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ለሁለት ዓመት በእስር ላይ ቆይተዋል።