በሆንግ ኮንግ በተደረገው ምርጫ የማዕከላዊ ቻይና መንግሥት ደጋፊ ዕጩዎች ድል ተቀዳጁ

መራጮች በሆንግ ኮንግ ምርጫ ጣቢያ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በሆንግ ኮንግ በተደረገው አወዛጋቢ በተባለውና በግዛቱ በታሪክ ዝቅተኛው የመራጮች ቁጥር በታየበት የሕግ አውጪ ምክር ቤት ምርጫ የማዕከላዊ ቻይና መንግሥት ደጋፊ የሆኑ ዕጩዎች በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፋቸውን ገለጹ።

ቻይና በግዛቲቱ ያወጣችው የደኅንነት ሕግ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ብሎም የሆንግ ኮንግ የምርጫ ሕግን ከቀየረች በኋላ የተደረገ የመጀመሪያው የሕግ አውጪው ምክር ቤት ምርጫ ነው።

የምርጫ ሕጉ ቤይጂንግ የእያንዳንዱን ዕጩ የጀርባ ታሪክ እንድትመረምር መብት የሚሰጥ ነው።

የግዛቲቱ ኃላፊዎች መረጋጋትን ለማምጣት ሲባል ምርጫው አስፈላጊ ነው ቢሉም ተቺዎች ግን ዴሞክራሲን ያዳከመ ሲሉ ገልጸውታል።

ኃላፊዎቹ እንዳሉት እድሜው ለመምረጥ ከደረሰው የግዛቲቷ ነዋሪ ውስጥ 30̀ በመቶ የሚሆነው ብቻ ድምጹን ሰጥቷል።

በተለምዶ ሌግኮ ወይም የሆንግ ኮንግ ትንሹ ፓርላማ ተብሎ የሚጠራው ይህ የሕግ አውጪ ምክር ቤት ከፍተኛ ሥልጣን ያለው ሲሆን በከተማዋ ሕግ ማውጣት እና ማሻሻልን ጨምሮ የተለያዩ ሥልጣኖች አሉት።

ምክር ቤቱ ካሉት አጠቃላይ 90 ወንበሮች ውስጥ 20ዎቹ ብቻ በሕዝብ ሲመረጡ 40ዎቹ በቤይጂንግ የምርጫ ኮሚቴ እንዲሁም ቀሪው 30 ደግሞ የልዩ ጥቅም ቡድን በሚባሉት እና በንግዱ ዓለም ውስጥ ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ቡድኖች የሚመርጡት ነው። በታሪክ እነዚህ የንግድ ማኅበራት ወደ ቤይጂንግ እንደሚያደሉ ይታወቃል።