የካፒቶል ሂል ሁከት፡ የአሜሪካ ፍርድ ቤት የትራምፕን ጥያቄ ውድቅ አደረገ

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ

የዩናይትድ ስቴትስ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የካፒቶል ሁከት መርማሪዎች የዋይት ሃውስ መዝገቦቻቸውን እንዳይመለከቱ ለማገድ ያቀረቡትን ጥያቄ ውድቅ አደረገው።

ትራምፕ በዋይት ሃውስ መዝገቦቻቸው የፕሬዝደንቶችን ማህደር በሚስጥር እንዲቀመጥ በሚፈቅደው መብት ሊጠበቅ ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል።

ሆኖም ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሰነዶቹ ላይ የነበረውን መብት አንስተዋል።

ትራምፕ ጥር 6 ስለተፈጠረው የካፒቶል ሂል ሁከት አስቀድመው ያውቁ እንደሆነ ለማወቅ ምርማሪዎች በምርመራ ላይ ይገኛሉ።

የአሜሪካ ኮንግረስ የጆ ባይደንን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት ለማረጋገጥ በስብሰባ ላይ ባለበት ወቅት የትራምፕ ደጋፊዎች ካፒቶል ህንጻን መውረራቸው ይታወሳል።

ትራምፕ ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ ምንም ማስረጃ ሳያቀርቡ መጨበርበር ነበር በሚል በባይደን መሸነፋቸውን ለመቀበል ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። የሐሙሱን ውሳኔን በመቃወም ይግባኝ ያቀርባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ጉዳዩም ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያመራል።

ውሳኔውን ያሳወቁት የኮሎምቢያ አካባቢ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ዳኞች የባይደንን ትዕዛዝ በመሻር የቀድሞው ፕሬዝዳንት ያቀረቡትን ጥያቄ የሚያስቀብል "ምንም ምክንያት" አላቀረቡም ብለዋል።

አክለውም ሁለቱም የመንግሥት አካላት ከጥቃቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው መዝገቦች ልዩ የህግ ፍላጎት እንዳለው ተስማምተዋል ብለዋል።

ጥያቄው በፕሬዝዳንት ባይደን ፓርቲ በሆነው ዴሞክራቶች የበላይነት በተያዘው በተወካዮች ምክር ቤት በተቋቋመ ኮሚቴ የተካሄደ ነው።

ኮሚቴው በኮንግረሱ ላይ ጥቃት ከመሰንዘሩ በፊት ስለነበረው ሁኔታ ፍንጭ ይሰጠኛል በሚል የስልክ ልውውጦችን፣ የጎብኝዎች መዝገቦችን እና ሌሎች የዋይት ሃውስ ሰነዶችን ለማየት ይፈልጋል።

"በቀድሞው እና በአሁኑ ፕሬዝዳንቶች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ሙሉ በሙሉ የመደመጥ ሕገ መንግሥታዊ እና ህጋዊ መብታቸው በመከልከልከሉ ሊጠገን የማይችል ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል" ሲሉ የትራምፕ ጠበቆች ደንበኛቸው ቀደም ሲል ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አቤት ብለዋል።

የካፒቶሉን ግርግር ተከትሎ አመጽ አነሳስተዋል በሚል ትራምፕ በኮንግረሱ የታችኛው ምክር ቤት ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳ ቢሆንም በወቅቱ ሪፐብሊካን በበላይነት በተቆጣጠሩት የላይኛው ምክር ቤት (ሴኔት) ውድቅ ሆኗል።

ከካፒቶል ሂልን አመጽ ጋር በተያያዘ ከ670 በላይ ሰዎች ታስረዋል።