ስቶከርዌር፡ አነጋጋሪ የሆኑት ባሎች ሚስቶቻቸውን የሚሰልሉባቸው የስልክ መተግበሪያዎች

ስልክ እና ላፕቶፕ ኮምፒዩተር እየተጠቀመች ያለች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማሪያ ጥብቅ በሆነ የካቶሊክ ቤተሰብ ሥር ነው ያደገችው።

ዘወትር እሑድ ተሰብስበው የቤተሰብ እራት ይበላሉ።

በተረጋጋ እና ቤተሰባዊ በሆነ መቀራረብ በሚያምኑ ወላጆች መሀል ነው ያደገችው።

ቤተሰብ መመሥረት ስትጀምር ወደፊት የምትመሠርተው ሕይወት ልክ እንደ ወላጆቿ እንዲሆን ነበር ምኞቷ።

ያሰበችው አልቀረም፣ ትዳር መሠረተች። አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ ተባባሉ።

ከቆይታ በኋላ ግን ዓይንህን ላፈር፣ ዓይንሽን ላፈር መባባሉ መጣ።

ባለቤቷ የሚመስለውን ዓይነት ሰው አልነበረም። ሕይወቷን በሙሉ ካልተቆጣጠርኩት አለ።

መጀመርያ አካባቢ ያንቋሽሻት ጀመር።

ቀጥሎ የገንዘብ እንቅስቃሴዋን በእርሱ ሥር አደረገ። ቀጥሎ ሦስት ልጆቻቸውን ከእርሱ ጋር አደረጋቸው።

ማሪያ ከሌሎች ሰዎች ጋር እንዳትገናኝ ሥራ እንዳስትሰራ በባሏ ተከለከለች፤ ኮምፒዩተር መጠቀም እንዳትችል አደረጋት።

ማሪያ ለ25 ዓመታት በዚህ የጭቆና ትዳር ውስጥ ቆየች። ሕይወቷን ገሀነም አደረገባት።

ከዚህ ጨቋኝ ባሏ ጋር መፋታት በራሱ ፈተና ሆነ።

ከዕለታት አንድ ቀን በቤተሰብ እርዳታ ጥላው ጠፋች።

አዲስ ሕይወት ለመጀመር ተፍ ተፍ ማለት ጀመረች።

አዲስ ፍቅረኛም ያዘች።

ነገር ግን አዲሱ ፍቅረኛዋ በእሷ ስም የስልክ መልዕክቶች በተደጋጋሚ ይደርሱታል። ግራ ተጋቡ።

እሷ መልዕክቱን እኔ አልላኩትም ትላለች። እሱ መልዕክቱ ከእሷ እንደሆነ የሚያረጋግጥ መልዕከት ይልክላታል።

እንዴት ሊሆን ቻለ? ይገረማሉ። የተለዋወጡት፣ ያወሩት ሁሉ መልሶ ይደርሳቸዋል።

ቀስ በቀስ ማሪያ የገባችበት ካፌ፣ የተራመደችበት ጎዳና፣ የተመገበችበት ሬስቶራንት ሁሉ የት እንደሆነ ይነገራት ጀመር።

የቀድሞ ባሏ በሄደችበት ሁሉ መከሰት ጀመረ።

አሁን በየትኛው ጎዳና ላይ የሚገኝ የእግረኛ መሻገሪያ እየተራመደች እንደሆነ የቀድሞ ባሏ ደውሎ ይነግራታል።

ባሰኘው ጊዜ ደግሞ ከመኪናዋ ኋላ እየነዳ ጡሩንባውን ያንባርቅባታል። ለእሷ ይህ እጅግ አስጨናቂ ጊዜ ነበር።

ሲያሰኘው ስልኳ ላይ ያስቀመጠችውን ፎቶ መልሶ ይልክላታል። እያንዳንዱ ምሥጢር የምትለው መረጃ ሁሉ እሱ ዘንድ ይደርሳል።

ከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ ትገባለች።

ይህ ሁኔታ ተደማምሮ ለከፍተኛ የአእምሮ ቀውስ ዳረጋት።

ነገሩን ተረጋግታ ስትመለከተው የቀድሞ ባሏ የስቶከርዌር የስልክ መተግበሪያ ተጠቃሚ እንደሆነ ደረሰችበት።

ባለሙያዎች ጥርጣሬን የሚፈጥሩ መተግበሪያዎችን በስልካችን ላይ ከተመለከትን እንድናጠፋው ይመክራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ባለሙያዎች ጥርጣሬን የሚፈጥሩ መተግበሪያዎችን በስልካችን ላይ ከተመለከትን እንድናጠፋው ይመክራሉ።

ስቶከርዌር ምንድነው?

ይህ የስልክ መተግበሪያ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውለው በደኅንነት ሰዎች ነው።

አሁን አሁን ግን ግለሰቦችም ሊኖራቸው እንደሚችል ታይቷል።

ይህን መተግበሪያ የሚጠቀም ሰው የሚከታተላትን ፍቅረኛውን ቁጥር በማስገባት ብቻ ሙሉ ሕይወቷን ሊቆጣጠረው ይችላል።

ይህም ማለት የምትለዋወጣቸውን የጽሑፍ መልእክቶች፣ ፎቶና ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በሙሉ ማየት ይችላል።

ይህ ብቻ አይደለም። ፍቅረኛው የቱ ጋር እንደሆነች የጂፒኤስ አድራሻ ማግኘት ይችላል።

ማሪያ ችግሩን ለመጋፈጥ ተነሳች። በተመሳሳይ ስቃይ የደረሰባቸውን ሰዎች አሰባስባ አንድ ማኅበር አቋቋመች።

ይህ ቡድን አሁን የስቶከርዌር መተግበሪያን መጠቀም ወንጀል እንዲሆን፣ በሕግ እንዲታገድ እየታገለ ይገኛል።

ይህ መተግበሪያ ከኮቪድ-19 የእንቅስቃሴ ገደብ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ ጥቅም ላይ እንደሚገኝ አንድ ጥናት ጠቁሟል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ይህን የስልክ መተግበሪያ እነ አፕልና ጉግል ስቶር ከክምችት ክፍላቸው እንዲያስወግዱት ጫናው በርትቶባቸዋል። እንደ ቫይረስ እንዲመለከቱትም ግፊት አይሎባቸዋል።

በጥቅምት ወር ጉግል በፍቅረኞች ላይ ስለላ የሚሠሩ መተግበሪያዎችን ብዙዎቹን ከክምችት ክፉሉ አራግፏል።

እነዚህ መተግበሪያዎች ብዙዉን ጊዜ ኢላማ የሚያደርጉት ወላጆችን ነው።

ወላጆች ደግሞ መተግበሪያዎቹ ያስፈልግጓቸዋል።

ልጆቻቸው የት እንደሚውሉ ለማወቅ ይህን መተግበሪያ እንዲጠቀሙ ይበረታታሉ።

ሆኖም ግን መተግበሪያዎቹ ባሎች በሚስቶቻቸው ላይ ስለላ እንዲያደርጉ የሚያበረታቱ ሆነው ተገኝተዋል።

ከእነዚህ መተግበሪያዎች አንዱ የሆነው ስፓይፎን (SpyFone) በአሜሪካ ፌዴራል የንግድ ኮሚሽን ሕገ ወጥ በሚል ከሥራ ውጪ ተደርጓል።

ምክንያቱም ያለ ሰዎች ፍቃድ መረጃን ለሁለተኛ ወገን ለቅሞ እንደሚያስተላልፍ ስለተደረሰበት ነው።

ይሁንና አሁንም በስልኮቻችን ውስጥ ምሥጢራዊ የግለሰብ መረጃን የሚያቀብሉ መተግበሪዎች ገበያውን አጥለቅልቀውታል።

እነዚህ መተግበሪያዎች ግለሰቦች የት እንደሚገኙ የ24 ሰዓት እንቅስቃሴያቸውን በድብቅ ለሌላ ወገን የሚያስተላልፉ መሆናቸው እጅግ ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩን ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።

በተለይም ሴቶችን በዚህ ረገድ ለጥቃት ተጋላጭ ያደርጋቸዋል።

ስልኮቻችን በስቶከርዌር መጠለፋቸውን ማወቅ ከናድ ሊሆን ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ስልኮቻችን በስቶከርዌር መጠለፋቸውን ማወቅ ከናድ ሊሆን ይችላል።

ስልኮቻችን በስቶከርዌር መጠለፋቸውን እንዴት እናውቃለን?

እነዚህ መተግበሪያዎች በቴክኖሎጂ በቂ ዕውቀት አላቸው የሚባሉ ሰዎችን ራሱ የሚፈትኑ ናቸው። የተሰሩበት መንገድም ቶሎ እንዲደረሰባቸው አያስችሉም።

ሻርለት በዚህ መተግበሪያ አማካይነት ችግር ውስጥ ከወደቁ ሴቶች አንዷ ናት።

እሷ እንደምትለው ስልኳ የሆነ ወቅት ላይ ያልተጠበቁ ባህሪዎችን ማሳየት ጀመረ።

ለምሳሌ ባትሪው ሙጥጥ ብሎ በፍጥነት ያልቃል። በራሱ ጊዜ ስልኳ ራሱን አጥፍቶ በድጋሚ ይነሳል።

በዚህን ጊዜ ነበር ወደ ባለሙያዎች ወስዳ ስልኳ በስቶከርዌር መጠለፉን ያረዷት።

ነገሩን ወደ ፀጥታ አካላት ስትወስደው ብዙም አልደነቃቸውም።

"ባል በሚስቱ ላይ መሰለል ችግር እንደሌለው የሚያስብ ባህል እንዳለ የገባኝ ያን ጊዜ ነው" ትላለች።

በኢንተርኔት ይህን ፍቅረኛን የማሰለል ሥራ እንደሚሠሩ የሚገልጹ በርካታ ድርጅቶች አሉ።

መተግበሪያውን ለመግዛት ግን ክፍያ በክሪፕቶከረንሲ ይጠይቃሉ።

ብዙዎቹ ሐቀኛ ባይሆኑም አንዳንዶቹ ይህን መተግበሪያ ለደንበኛ እንደሚያቅርቡ ተደርሶበታል።

ይህን ችግር ስፋትና አደጋውን ተከትሎ አሁን በርካታ አገራት እነዚህን መተግበሪያዎች በሕግ እያገዷቸው ይገኛሉ።

ለምሳሌ ፈረንሳይ በ2020 ማንኛውንም በሴቶች ላይ የሚደርስ የቤት ውስጥ ጥቃት የሚያበረታቱ እንደነዚህ ያሉ የስልክ መተግበሪያዎችን በወንጀል የሚያስጠይቁ አድርጋ ደንግጋዋለች።

እነዚህን መተግበሪያዎች በፈረንሳይ ሲጠቀም የተገኘ በአንድ ዓመት እስራት እና የ45 ሺህ ዩሮ ቅጣት ይጠብቀዋል።

ባለሙያዎች ግን ከዚህም በላይ እርምጃ መወሰድ አለበት ይላሉ።

በተለይ ጉግልና አፕል እንዲህ አይነት መተግበሪያዎች በስልኮቻቸው እንዳይጫኑ መመሪያ ካላስተላለፉ ችግሩ እየባሰ እንጂ እየተሻሻለ አይመጣም ባይ ናቸው።