አሌክ ባልድዊን ከድንገተኛው ተኩስ በኋላ የፊልም ሙያ ህይወቱ ሊያከትም እንደሚችል ተናገረ

ታዋቂው አሜሪካዊ የፊልም ተዋናይ አሌክ ባልድዊን በቅርቡ በነበረ የፊልም ቀረፃ ላይ የፎቶግራፍ ዳይሬክተሯ ሃሊና ሁቺንስን በድንገት ተኩሶ መግደሉን ተከትሎ የፊልም ሙያ ህይወቱ ሊያከትም እንደሚችል ተናገረ።

የ63 አመቱ ተዋናይ ከኤቢሲ ኒውስ ጋዜጠኛው ጆርጅ ስቴፋኖፖሎስ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ "የፊልም ሙያ ህይወቴ ሊያከትም ይችላል" ካለ በኋላ ግድ እንደሌለው ተናግሯል።

አሌክ ባልድዊን ባለፈው ወር በኒው ሜክሲኮ በተፈጠረው ክስተት የሽጉጡን ቃታ አልሳብኩም ያለ ሲሆን "አንድ ሰው ሽጉጡን አቀባብሎታል ።እኔ እንዳልሆንኩ አውቃለሁ"

ተዋናዩ 30 ሮክ በተባለ የኮሜዲ ፊልም እንዲሁም የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን በቅዳሜ ምሽት የቀጥታ ስርጭት ላይ በማስመሰል ከፍተኛ ዝናን አትርፏል።

የኤቢሲ ቃለ ምልልስ የተሰራጨው በያዝነው ሳምንት ሃሙስ አመሻሽ ላይ በአሜሪካ ነው።

"በዚያ ቀረፃ ላይ ምን እንደተፈጠረ አላውቅም። ያ ጥይት እንዴት ሽጉጡ ውስጡ እንዴት እንደገባም ሆነ እንዴት እንደተቀባበለ አላውቅም። እኔ አላውቅም" ሲል ባልድዊን ተናግሯል።

"ነገር ግን ይህ እንደገና የመከሰት ዕድሉ አነስተኛ ወደ ሆነበት ቦታ የሚወስደንን ማንኛውንም ሁኔታ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ" ሲል አስረድቷል።

ተዋናዩ በጥቅምት ወር ላይ በነበረው የቀረፃ ልምምድ ላይ ህይወቷ ያለፈው የፎቶግራፍ ዳይሬክተሯ ሃሊና ሁቺንስን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ እየመራች ነበር ብሏል።

"በቀረፃው ላይ ሽጉጡን እንዴት መያዝ እንዳለብኝ እያሳየችኝ ነበር" የሚለው ተዋናዩ "ሽጉጡን እንድይዝ በነገረችኝ መንገድ ነው የደገንኩት እናም በመጨረሻም ሳላውቀው በብብቷ ስር ተተኮሰ" ብሏል።

ተኩሱን በፊልሙ ላይ ለማስመሰል የሽጉጡ ቃታን እንደሳብኩት ማስመሰል ነበረብኝ እናም መተኮስ አልነበረብኝም።

"ቃታው አልተሳበም። ቃታውን አልሳብኩትም" ብሏል።